ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | መከላከያ ሀዋሳን በመርታት ዙሩን አገባዷል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ዘጠነኛ ሳምንት የመጀመርያ ጨዋታ በሀዋሳ እና መከላከያ መካከል ተደርጎ መከላከያ 2 ለ 1 አሸናፊ ሆኗል፡፡ 

ቀደም ብሎ ብርቱ ፉክክር ይስተናገድበታል ተብሎ ቢጠበቅም የመከላከያ ብልጫ ከተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎች ጋር ሲያደርጉ የተመለከትንበት በተለይ የመጀመሪያው አጋማሽ መገለጫ ነበር፡፡ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል ለመድረስ ሲቸገሩ ያልታዩት መከላከያዎች ባደረጓቸው አስገራሚ ሙከራዎች ታግዘው 16ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አስቆጥረዋል፡፡

የሀዋሳዋ ግብ ጠባቂ ዓባይነሽ ኤርቄሎ ኳስ ይዛ በምስታጀምርበት ወቅት ከተከላካይዋ ቅድስት ዘለቀ ጋር ባለመናበቧ በሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ በመንካቷ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ሴናፍ ዋቁማ ወደ ጎልነት ለውጣው መከላከያ ቀዳሚ ሆኗል፡፡ በቀሩት ደቂቃዎች ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር መከላከያ ብልጫን ወስደው የተጫወቱ ሲሆን ካለፉት ጨዋታዎች ዛሬ ሜዳ ላይ ደከም ብለው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች መሳይ ተመስገን ከርቀት በምታደርገው ያልተሳኩ ሙከራዎች ጎሎችን ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም ጠጣር የነበረውን የመከላከያን የተከላካይ ክፍል መፈተን ሳይችሉ 1 ለ 0 በመከላከያ መሪነት የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ከቀዳሚው አርባ አምስት በተወሰነ መልኩ መነቃቃት ይታይባቸው ሀዋሳዎች ምንም እንኳን ወደ ጨዋታ ቅኝት መግባት ቢችሉም ጎል ላይ ያላቸው ደካማ የውሳኔ አሰጣጥ ጎልቶ የታየበት ነበር፡፡ በአንፃሩ መከላከያዎች በእንቅስቃሴ ጥሩ መሆን ቢችሉም ወደ ፊት ለመጠጋት ግን ከመጀመሪያው አጋማሽ ተቀዛቅዘው ታይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ዐይዳ ዑስማንን ቀይረው ወደ ሜዳ ከገቡ በኃላ አጥቂዋ ጥንካሬ የከዳው የሀዋሳ ተከላይ መስመርን ስትረብሽ ውላለች። በዚህም ከቅጣት ምት ከርቀት ካደረገችው ሙከራ አራት ደቂቃዎች መልስ ማለትም 58ኛው ደቂቃ ላይ ሴናፍ ከቀኝ አቅጣጫ በረጅሙ ያሻገረችውን ኳስ ስህተቶች በተደጋጋሚ ሲታይባት የነበረችው ዓባይነሽ ኤርቄሎ በቀላሉ መያዝ የምትችለውን በመዘናጋቷ ዐይዳ ዑስማን ዘላ ኳሱን በመንጠቅ ሁለት ጊዜ ገፋ ካደረገች በኃላ በድንቅ አጨራረስ ሁለተኛ ጎል ለቡድኗ አስቆጥራለች፡፡

በቀሩት ደቂቃዎች ክፍተት ይታይባቸው እንጂ ቶሎ ቶሎ ጎል ለማስቆጠር ጫና ሲያሳድሩ የታዩት ሀዋሳዎች በነፃነት መና እና መሳይ ተመስገን አማካኝነት ወደ ጎል ቀርበዋል፡፡ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በተጠናቀቀበት ቅፅበት ተቀይራ የገባችው ዓይናለም አሳምነው መሀል ለመሀል የሰጠቻትን ኳስ መሳይ ተመስገን በአግባቡ ተጠቅማ ሀዋሳ ከሽንፈት ያልታደገች ጎል ከመረብ አሳርፋለች፡፡ አቻ ለመሆን ጥረት ያልተለያቸው ሀዋሳዎች ተጨማሪ ግብን ሳያገኙ ጨዋታው በመከላከያ 2 ለ 1 አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ልሳን የሴቶች ስፖርት የመከላከያዋን ተጫዋች ሥራ ይርዳውን የጨዋታው ምርጥ በማለት ሸልሟታል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ