“ክለቡ ያለበትን ሁኔታ እረዳለው” አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው

ከደሞዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ በቅርቡ ራሳቸውን ከጅማ አባ ጅፋር አሰልጣኝነት ያገለሉት አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ስላልተጠበቀ ውሳኔያቸው ይናገራሉ።

ምንም እንኳን ክለቡ በአሰልጣኙ ቅሬታ ዙርያ ጥርት ያለ ምላሽ ባይሰጥም አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው የሰባት ወር ደሞዝ እና የፊርማ ገንዘብ አልተከፈለኝም በማለት ከሳምንት በፊት ራሳቸውን ከጅማ አባ ጅፋር አሰልጣኝነት አንስተው ለፌዴሬሽኑም ሆነ ለክለቡ “ደሞዝ ካልተከፈለኝ አልሰራም” በማለት የቅሬታ ደብዳቤያቸውን ማስገባታቸው ይታወቃል። ይህን ተከትሎ ክለቡ እስካሁን በምክትል አሰልጣኝ እየተመራ ይገኛል። አሰልጣኝ ጳውሎስ ያስገቡት ደብዳቤ እና ሒደቱ በምን ሁኔታ ይገኛል ስንል አናግረናቸው ያልተጠበቀ ውሳኔያቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ አሳውቀዋል።

” ያለ ደሞዝ ለወራት መስራት በጣም ከባድ ነው። ይህን ሁሉ ጊዜ በትዕግስት የጠበቅኩት ክለቡን እና የጅማ ህዝብ ደጋፊዎችን ስለምወድ እና ስለማከብር ነው። ችግሩ ይቀረፋል ብዬ ብጠብቅም ሊሆን ስላልቻለ እና ከነችግሩ መቆየት የቤተሰብ ኃላፊ እንደመሆኔ መጠን ከባድ በመሆኑ ክለቡን እየወደድኩት ለመለያየት ችያለው። ክለቡ ያለበትን ሁኔታ እረዳለሁ። የሠራሁበት ክለብ ነው፤ ገንዘብ ቢኖራቸው ይከፍሉኝ ነበር። ክለቡን ከስሼ ጥቅሜን እንደማስከብር ባውቅም ሁሉን ነገር ትቼ በፍቅር በስምምነት መለያየትን ወስኛለው። ይህን ያደረኩት የጅማን ህዝብ እና ደጋፊዎችን ስለምወድ ነው። በቅርቡ በአንድ ክለብ ዳግም ወደ ሥልጠናው እመለሳለው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ