ሪፖርት | ወልቂጤ ከተማ ወደ ድል ተመልሷል

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አስረኛ ሳምንት ዛሬ መካሄድ ሲጀምር ረፋድ ላይ ድሬዳዋ ከተማን የገጠመው ወልቂጤ ከተማ 3-1 አሸንፏል።

ድሬዳዋ ከተማ አዳማን ከረታበት ጨዋታ ፍቃዱ ደነቀን በያሬድ ዘውድነህ ብቻ በመቀየር ለዛሬው ጨዋታ ሲቀርብ በወልቂጤ በኩል ተስፋዬ ነጋሽ ፣ አህመድ ሁሴን ፣ ፍሬው ሰለሞን እና ሀብታሙ ሸዋለምን በሥዩም ተስፋዬ፣ አሳሪ አልመሀዲ፣ አቡበከር ሳኒ እና ተስፋዬ መላኩ ተክተው ገብተዋል።

የጨዋታው ማስጀመያ ፊሽካ በተሰማበት ቅፅበት ድሬዳዋ ከተማዎች በሰነዘሩት ፈጣን ጥቃት መሪ ለመሆን በእጅጉ ቀርበው ነበር። ጁኒያስ ናንጄቦ ከቀኝ መስመር ያመቻቸውን ኳስ ሱራፌል ጌታቸው መትቶ ጀማል ሲመልሰው አስቻለው ግርማ ያልተጠቀመበት ኳስ የድሬ አስቆጪ ሙከራ ነበር።

ተነቃቅቶ የጀመረው ጨዋታ ቀጥሎ ወልቂጤዎች ከግራ መስመር ረመዳን ያሻገረውን ኳስ አቡበከር ሳኒ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ውጪ በወጣበት ሙከራ የጎል ዕድል የፈጠሩ ሲሆን ከአስር ደቂቃ በኋላ ደግሞ በድሬዎች በኩል ሙኽዲን ሙሳ ከቀኝ መስመር የመታው ኳስ ወደ ውጪ ወጥቷል።

በሒደት እየተቀዛቀዘ የመጣው ጨዋታው በቀሪዎቹ የመጀመርያ አጋማሽ ደቂቃዎች የጎል ዕድል ያልተፈጠረበት ይልቁንም ጥፋቶች የበዙበት ነበር። በዚህም ከቅጣት መልስ ጨዋታ ያደረገው አልሳሪ አልመሐዲ በጉዳት ገና በሠላሳኛው ደቂቃ በአሜ መሐመድ ተቀይሮ ወጥቷል። ተቀይሮ የገባው አሜ መሐመድም ከአስር ደቂቃዎች በኋላ ጎል አስቆጥሮ ወልቂጤ መሪ ሆኖ ወደ እረፍት እንዲያመራ አድርጓል። ረመዳን የሱፍ በድንቅ ሁኔታ ወደ ሳጥን በመግባት ያሻገረለትን ኳስ ነበር አሜ ያስቆጠረው።

በሁለተኛው አጋማሽ ወልቂጤዎች ለማጥቃት የተሻለ ክፍተት ማግኘታቸውን ተከትሎ የጎል ዕድሎችን መፍጠር የቻሉ ሲሆን በ49ኛው ደቂቃ አቡበከር ሳኒ ከሄኖክ አየለ የተሻገረለትን ጥሩ ኳስ ከጎል ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ያመከነው የሚጠቀስ ነበር። አቡበከር ይህንን ወርቃማ አጋጣሚ ካመከነ አስር ደቂቃዎች በኋላ ከአሜ መሐመድ የተመቻቸለትን ኳስ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል መትቶ የግብ ጠባቂው ፍሬው ስህተት ታክሎበት ለወልቂጤ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል።

በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ ለመንቀሳቀስ የሞከሩት ድሬዎች ከናንጄቦ ኢላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ውጪ ለረጅም ደቂቃዎች የጠራ የጎል ዕድል መፍጠር ባይችሉም በ75ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጪ ሙኽዲን ሙሳ በግሩም ቮሊ ባስቆጠረው ጎል ወደ ጨዋታው ተመልሰዋል። በቀሩት ደቂቃዎችም ጫና መፍጠር የቻሉ ሲሆን በ86ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተመታ ኳስ ሲመለስ ዳንኤል ደምሴ በሞከረውና ጀማል ባወጣበት ኳስ አቻ ለመሆን እጅጉን ቀርበው ነበር።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በመልሶ ማጥቃት ወደ ድሬዳዋ የጎል ክልል የደረሱት ወልቂጤዎች በጭማሪ ደቂቃ ላይ ሄኖክ ያመቻቸለትን ግልፅ የጎል ዕድል አሜ ቢያመውነውም ከደቂቃ በኋላ አብዱልከሪም ወርቁ ከፍሬዘር የቀማውን ኳስ በተረጋጋ አጨራረስ አስቆጥሮ ጨዋታውን 3-1 በሆነ አሸናፊነት አጠናቀዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ