ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አስረኛ ሳምንት ቁጥሮች እና ዕውነታዎች

በአስረኛው ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በተከናወኑ ስድስት ጨዋታዎች ላይ የተመዘገቡ ቁጥራዊ መረጃዎችን በሚከተለው መልኩ አጠናቅረናል።

– በዚህ ሳምንት በተደረጉ ስድስት ጨዋታዎች 16 ጎሎች ተቆጥረዋል። ይህም በጎል ድርቅ ተመትቶ ከነበረው ያለፈው ሳምንት በእጥፍ የላቀ ነው።

– ከተቆጠሩት 16 ጎሎች ገሚሱ (ስምንት) በመጀመርያ አጋማሽ ሲቆጠሩ ገሚሱ (ስምንት) በሁለተኛው አጋማሽ ተቆጥረዋል።

– ወልቂጤ፣ አዳማ እና ድቻ ሦስት ጎሎች በማስቆጠር የሳምንቱን ከፍተኛ ቁጥር አስመዝግበዋል።

– ከተቆጠሩት 16 ጎሎች መካከል ሁለት በፍፁም ቅጣት ምት (አቡበከር ናስር እና ብሩክ በየነ)፣ አንድ ቅጣት ምት (መላኩ ወልዴ) እና ሁለት መነሻቸው ከማዕዘን ምት የሆኑ (አንተነህ ጉግሳ እና ደጉ ደበበ) ጎሎች ሲቆጠሩ 11 ጎሎች በክፍት ጨዋታ ተቆጥረዋል።

– መላኩ ወልዴ፣ ሚኪያስ መኮንን እና ሙኽዲን ሙሳ ከሳጥን ውጪ ጎል ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው። ሌሎቹ 13 ጎሎች የተቆጠሩት ከሳጥን ውስጥ ተመትተው ነው።

– አብዲሳ ጀማል፣ ደጉ ደበበ እና አንተነህ ጉግሳ በግንባር በመግጨት ጎል ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ሲሆኑ ሌሎቹ ጎሎች የተቆጠሩት በእግር ተመትተው ነው።

– 14 ተጫዋቾች በዚህ ሳምንት ጎል አስቆጥረዋል። አብዲሳ ጀማል በሦስት ጎሎች ቀዳሚ ሲሆን ሌሎቹ አንድ አንድ አስቆጥረዋል።

– ስምንት ተጫዋቾች በዚህ ሳምንት የዓመቱ የመጀመርያ ጎላቸውን አስቆጥረዋል። አንተነህ ጉግሳ፣ ደጉ ደበበ፣ መሳይ አገኘሁ፣ ሚኪያስ መኮንን፣ አሜ መሐመድ፣ አቡበከር ሳኒ እና አብዱልከሪም ወርቁ ተጫዋቾቹ ናቸው።

– 9 ተጫዋቾች ለቡድን አጋሮቻቸው ጎል የሆነ ኳስ በማመቻቸት ተሳትፈዋል። መሳይ አገኘሁ በሁለት ኳሶች ቀዳሚ ነው።

– በጎልም በማመቻቸትም የተሳተፉ ተጫዋቾች ሁለት ናቸው። መሳይ አገኘሁ (1 ጎል እና 1 አሲስት) እና አሜ መሐመድ (1 ጎል እና 1 አሲስት)

– አቡበከር ናስር አምስተኛ ተከታታይ ጨዋታ ላይ ጎል አስቆጥሮ ወጥቷል። ለሙኅዲን ሙሳ ደግሞ ሁለተኛ ተከታታይ ጨዋታ ጎሉ ነው።

– ዳዋ ሆቴሳ በዚህ ሳምንት የፍፁም ቅጣት ምት ያመከነ ተጫዋች ሆኗል።

– ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ግብ ጠባቂው ለዓለም ብርሀኑ ለተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ጎል ሳያስተናግዱ ወጥተዋል።

– ኢትዮጵያ ቡና ባደረጋቸው ሁሉም ጨዋታዎች ጎል እያስተናገደ የወጣ ብቸኛ ቡድን ሆኗል።

– አዳማ ከተማ ከሰባት ጨዋታ በኋላ ድል ሲያስመዘግብ ሀዋሳ ከተማ ከአምስት ሽንፈት አልባ ጨዋታዎች በኋላ ሽንፈት አስተናግዷል።

የዲሲፕሊን ቁጥሮች

– በዚህ ሳምንት ለ26 ተጫዋቾች እና ለ1 አሰልጣኝ (ዘርዓይ ሙሉ) ቢጫ ካርዶች ተመዘዋል።

– 7 ካርዶችን የተመለከተው ሲዳማ ቡና ቀዳሚውኝ ስፍራ ሲይዝ ጅማ አባ ጅፋር፣ ባህር ዳር ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ካርድ ያልተመለከቱ ቡድኖች ናቸው።

– ፈቱዲን ጀማል (ሁለት ቢጫ)፣ ተክለማርያም ሻንቆ እና የአዳማ ከተማው የህክምና ባለሙያ ዮሐንስ ጌታቸው (ሁለት ቢጫ) በዚህ ሳምንት የቀይ ካርድ የተመለከቱ ናቸው።


© ሶከር ኢትዮጵያ