“… የመጣሁበት መንገድ ይህ ይመስለኛል” – ደጉ ደበበ

ለብዙ እግርኳሰኞች ምሳሌ መሆን የሚችለው ደጉ ደበበ ከድረገፃችን ጋር ቆይታ አድርጓል።

በሊጉ በወጥ አቋም በማሳየት እስካሁን መድመቁን ቀጥሏል። በአርባምንጭ ጨርቃ ጨርቅ የጀመረው የእግርኳስ ህይወቱ በቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ብሔራዊ ቡድን እና ወላይታ ድቻ ቀጥሎ ለሁለት አስርት ዓመታት ዘልቋል።

አምስት ጊዜ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን በአምበልነት በማንሳት ባለታሪክ የሆነው ደጉ ሁለት ጊዜ የሊጉ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ተመርጧል። የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ፣ ሁለት የሴካፋ ዋንጫዎች፣ አስር የፕሪምየር ሊግ፣ ሦስት የኢትዮጵያ ዋንጫ እና አምስት አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫዎችን ጨምሮ በስኬት ያሸበረቁ የተጫዋችነት ዘመናት እያሳለፈ የሚገኘው ደጉ ደበበ አሁንም እንደ ወይን እያደረ መጣፈጡን ቀጥሎ ዘንድሮም ወላይታ ድቻን በአምበልነት እየመራ በመደበኝነት እየተጫወተ ይገኛል።

በዛሬው ጨዋታ ጎል ያስቆጠረው ባለ ከፍተኛ ልምዱ ደጉ ስለ ጎሉ እና ሌሎች ጉዳዮች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል።

የመጀመርያ የሊጉ ጎልህን ታስታውሰዋለህ ?

ኡ…! በጣም ከባድ ነው። አሁን ማስታወስ አልችልም። በ1994 አርባምንጭ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሲገባ በርከት ያሉ ጎሎችን እንዳስቆጠርኩ አውቃለሁ። የመጀመርያ ጎሌን ማስታወስ ይቸግረኛል። ብቻ ከመሳይ ተፈሪ ቀጥሎ ጎል በርካታ ጎሎች አስቆጥር ነበር። ምክንያቱም በጊዜው ከአጥቂ ጀርባ እጫወት ነበር።

እንዴት ወደ ተከላካይነት መጣህ ?

አዱኛ ገላነት የሚባል ተከላካይ ነበር። የመኮንን ገላነህ (ዊሀ) ወንድም፤ እርሱ በአጋጣሚ ሆኖ ሲጎዳ ወደ ኃላ ተመልሼ ለመጫወት ችዬ ነው በዛው ተከላካይ ሆኜ የቀረሁት።

ይሄን ያህል ዓመት በጥንካሬ የመዝለቅህ ሚስጢር ምንድነው ?

የምትወደውን ነገር በአግባቡ መያዝ ማክበር እና መሥራት ነው። በትንሽ ነገር አለመርካት እና ጠንክሮ መሥራት ይመስለኛል።

የወላይታ ድቻ ወቅታዊ አቋምን እንዴት ታየዋለህ ?

ቡድናችን ከአዲስ አበባ በኃላ ወደ ጅማ ከመጣ ጀምሮ መሻሻሎችን እያሳየ ይገኛል። ጅማ ከመጣን ካደረግናቸው አራት ጨዋታዎች ሰባት ነጥብ አግኝተናል። ይህ ወደ ጅማ ከመጣን በኃላ የተሻለ ውጤት እያስመዘገብን መሆኑን ማሳያ ነው። አሁን ጥሩ ቅርፅ እየያዘ ነው። በቀጣይ ከእረፍት መልስ የተሻለውን ድቻን እናያለን።

ደጉ እግርኳስ መጫወትን አልጠገበም ?

ከእግርኳስ መለየት ከባድ ነው። የምትወደውን ነገር ማጣት አስቸጋሪ ነው። እግርኳስ እየወደድከው እየተዝናናህ የምትሰራው ሙያ ነው። ስለዚህ ከእግርኳስ መራቅ ይከብዳል። የኛ ሙያ ፊት ለፊት ሜዳ ላይ የሚታይ ስለሆነ አቅሜ እስከፈቀደ ድረስ እጫወታለሁ። መሥራት ካልቻልክ አቅምህ ይነግርሀል፤ የሚታይ ስለሆነ። ካልቻልክ የምታቆመው ይሆናል።

ትውልዱ ከአንተ እንዲማር ምን ትመክራለህ ?

ቅድም እንዳነሳሁት የምትወደውን ነገር በአግባቡ መያዝ፣ ላመንክበት ለምትወደው ሙያ ጠንክሮ መሥራት ያስፈልጋል። ሙያህ ከእጅህ ወጥቶ እንዳይበላሽ ሁሌም ራስን ማዘጋጀት ይገባል። እኔ ሙያዬን እወዳለሁ። ሙያዬ እንዲበላሽብኝ አልፈልግም። ሁልግዜም ጠንክሬ ነው የምሰራው። የመጣሁበት መንገድ ይሄ ይመስለኛል። አሁን ያለው ትውልድም ይሄን መንገድ ቢከተል መልካም ነው። አስፈላጊም ነገር ነው፤ የምትወደውን ነገር በአግባቡ መያዝ። ሙያውን መውድድ ማክበር ይገባል እላለሁ።

*ከድቻ ጋር ያለው ኮንትራት ከቀናት በኃላ የሚጠናቀቀው ደጉ ደበበ ከክለቡ ጋር ኮንትራቱን ስለማራዘም እየተደራደረ እንደሆነ ሰምተናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ