ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

በአስረኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ትኩረት ያገኙ ተጫዋች ነክ ጉዳዮችን እንደሚከተለው አሰናድተናል።

👉ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን ያሳየው አሜ መሐመድ

በኢትዮጵያ እግርኳስ እንዳለመታደል ሆኖ ተስፈኛ ተጫዋቾች መልካም አጀማመርን በከፍተኛ ደረጃ እግር ኳስ አድርገው ዕድገታቸውን ግን ለማስቀጠል ሲቸገሩ መመልከት የተለመደ ነው። ከጥቂት ዓመታት በፊት በ2008 እና በ2009 በከፍተኛ ሊጉ ጅማ አባ ቡና ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመምጣት ባለፈበት ሒደት ውስጥ ተሳክቶለት ሊጉን ከተቀላቀለ በኃላ በዛው ቢመለስም አሜ መሐመድ በቡድኑ ውስጥ የነበረው የጎላ ድርሻ በቀላሉ የሚታይ አልነበረም።

ፈጠን ያለ ዕድገትን እያሳየ የነበረው የመሐል እና የመስመር አጥቂ በ2010 ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ካመራ ወዲህ ግን እንደተጠበቀው ራሱን ማሳየት ሳይችል በተደጋጋሚ ጉዳቶች እና የጨዋታ ደቂቃዎች እጦት በታየበት የአቋም መውረድ ያለፉትን ሦስት ዓመታት በጊዮርጊስ ቤት ተስፋ አስቆራጭ ጊዜያትን ማሳለፉ አይዘነጋም።

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ተጫዋቹ ፈረሰኞቹን ለቆ ወደ ወልቂጤ ከተማ አምርቶ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ጨዋታዎች የመሰለፍ ዕድልን ቢያገኝም አመርቂ እንቅስቃሴ ማድረግ ባለመቻሉ ወደ ተጠባባቂነት ለመውረድ ተገዷል። ነገርግን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በአስገዳጅ ቅያሪ በ30ኛው ደቂቃ ጉዳት ያስተናገደው አልሳሪ አልመህዲን ተክቶ ወደ ሜዳ የገባው አሜ ከአስር ደቂቃ የሜዳ ላይ ቆይታ በኃላ ቡድኑን መሪ ያደረገችን ግብ ማስቆጠር ሲችል በሁለተኛው አጋማሽም አቡበከር ሳኒ ላስቆጠራት ሁለተኛ ግብ ኳሷን አመቻችቶ በማቀበል ውጤታማ የጨዋታ ዕለትን አሳልፏል።

ይህም አጋጣሚ ራሱን ፈልጎ ለማግኘት እየታተረ ለሚገኘው ተጫዋቹ እንደ ጥሩ መነሳሻ በመጠቀም በቀጣይ ጨዋታዎች የተሻለ እንቅስቃሴ ለማድረግ እንደ መነሻነት ሊጠቀምበት ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።

👉 ምስጉኑ ተክለማርያም ሻንቆ እና የስሜታዊው ፈቱዲን ጀማል ያልተገባ ድርጊት

በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ ተጫዋቾች ከቡድናቸው በተቃራኒ በዳኞች የሚወሰኑ ውሳኔዎች በመቃወም ዳኞችን መክበብ እና ማዋከብ የተለመደ ነው። በተለይም ውሳኔዎቹ ፍፁም ቅጣት ምት አልያም ካርድ የሚያስመስዙ ከሆነ ሁኔታውን ይበልጥ የከፍ ያደርገዋል። ከዚህ በተቃራኒ በዳኞች የሚተላለፉ ውሳኔዎችን በፀጋ የሚቀበሉ ተጫዋቾችን ግን ፈልጎ ማግኘቱ እጅግ ከባድ ያደርገዋል። ነገርግን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በሊጉ ከዚህ አንፃር በምሳሌነት የሚጠቀስን በጎ ተግባርን የኢትዮጵያ ቡናው ግብጠባቂ ተክለማርያም ሻንቆ ፈፅሞ ተመልክተናል።

ኢትዮጵያ ቡና ከባህርዳር ከተማ ጋር 2-2 በተለያዩበት ጨዋታ መገባደጃ ደቂቃዎች ወደ መሀል ሜዳ ተጠግቶ ከሚከላከለው የኢትዮጵያ ቡና የተከላካይ መስመር ጀርባ የተጣለን ኳስ ለመቆጣጠር ከግብ ክልሉ በፍጥነት ለቆ የወጣው ተክለማርያም ሻንቆ ኳሱን ለመቆጣጠር በሞከረበት ወቅት ኳሷ ነጥራ እጁን በመንካቷ ተጫዋቹ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ለመወገድ ተገዷል። ተጫዋቹም በቀጥታ የተመዘዘበትን የቀይ ካርድ እምብዛም ሲደረግ ባልተለመደ መልኩ በፀጋ ተቀብሎ ዳኛውን አቅፎ ከሜዳ ያለንትርክ የወጣበት መንገድ የሚያስመሰግን ተግባር ነው።

በተቃራኒው ሲዳማ ቡናን በአምበልነት እየመራ ወደ ሜዳ የገባው ፈቱዲን ጀማል ቡድኑ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባደረገው እና 0-0 በተጠናቀቀው ጨዋታ ላይ የፈፀው ተግባር ደግሞ ከእሱ የማይጠበቅ ነበር። ምንም እንኳን የቡድኑ አምበል ቢሆንም ጥፋት ተፈፅሞ የጨዋታው እንቅስቃሴ በቆመበት ቅፅበት የዳኛን ውሳኔ በመቃወም የቢጫ ካርድ ሰለባ የሆነው ተጫዋቹ የቢጫ ካርድ መመልከቱ ከድርጊቱ ሊያርመው ሲገባ ይባስ ብሎ ከዳኛው ጋር ከረር ያለ ክርክር እንዲሁም ሰጣ ገባ ውስጥ በመግባቱ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ሊወገድ ችሏል።

ይባስ ብሎ ከሜዳ በሚወጣበት ወቅትም በስላቅ ስሜት ለውሳኔው ያሳየው የጭብጨባ አፀፋ ተጫዋቹን ይበልጡኑ ትዝብት ውስጥ የከተተ ድርጊት ነበር።

👉ግብ ጠባቂዎችን የሚቀያይረው አዳማ ከተማ

ፕሪምየር ሊጉ የመጀመሪያው ዙር ሊጠናቀቅ ጥቂት የጨዋታ ሳምንታት ብቻ ቀርተውታል። 10ኛ የጨዋታ ሳምንቱን ባጠናቀቀው ሊጉ በቀደመው አስፈሪነቱ ላይ የማይገኘው አዳማ ከተማ በዚህ የጨዋታ ሳምንት ባስመዘገበው ድል ታግዞ በሰባት ነጥብ በ12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

እስካሁን ድረስ በሊጉ ዘጠኝ ጨዋታዎች ያደረገው አዳማ ከሁሉም የሊጉ ተካፋይ ቡድኖች በተለየ በስብስቡ ውስጥ የያዘቸውን ሦስቱንም ግብ ጠባቂዎች ተጠቅሟል። በሊጉ በተለያዩ ክለቦች በግብጠባቂነት ያገለገለው ታሪክ ጌትነት ፣ ለረጅም ዓመታት በተጠባባቂነት በአዲስ አበባ ከተማ እና አዳማ የቆየው ዳንኤል ተሾመን እና ከከፍተኛ ሊግ የተዘዋወረው ኢብሳ አበበን የያዘው ቡድኑ በእስካሁኑ የአስር ሳምንት ጉዞ ለእያንዳንዳቸው ቢያንስ ሁለት እና ከዚያ በላይ የሆኑ ጨዋታዎች ላይ ግቦቹን እንዲጠብቁ አድርጓል።

እርግጥ ነው በተወሰኑት ጨዋታዎች በቀደመው ጨዋታ በግብ ጠባቂነት የጀመሩ ተጫዋቾች በጉዳት ቀጣዩን ጨዋታ መጀመር አለመቻላቸው በቡድኑ አሰልጣኝ ቢገለፅም ከብቃት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ሊኖሩ እንደሚችሉም ይገመታል።

ከቡድኖች ውጤታማነት በስተጀርባ በርካታ ጉዳዮች በምክንያትነት ይቀርባሉ፤ ከእነዚህም መካከል ከጨዋታ ጨዋታ የሚኖር የስብስብ ወጥነት አንዱ ነው። በዚህ ሂደት የሚፈጠረው የቡድን ውህደት እና መግግባት ለቡድኖች እጅግ ጠቃሚ ነው። ነገር ግን በአዳማ ከተማ በቡድኑ አከርካሪ በተለይም ግብ ጠባቂ ስፍራ ላይ የሚደረጉ ተደጋጋሚ ለውጦች ይህንን ጥቅም እያሳጡት ይገኛሉ።

👉የተፋዘዘውን አዳማ ከተማን ያነቃቃው አብዲሳ ጀማል

አዳማ ከተማዎች በሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት መርሐግብር በተጨዋቾች ስብስብ ያልተሟላ የነበረውን እና በቀይ ካርድ ሳቢያ የሜዳ ላይ ተጨዋችን ግብ ጠባቂ ለማድረግ የተገደደው ጅማ አባ ጅፋርን ከረቱበት ውጤት ወዲህ ባደረጓቸው ጨዋታዎች አንድ የአቻ ውጤት በማስመዝገብ በድምሩ አራት ነጥብ በመሰብሰብ ከሊጉ ግርጌ በአንድ ከፍ ብለው 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በዚህ አስከፊ የውጤት ማጣት ውስጥ በከረመው ቡድን ውስጥ በተለይ አጥቂው አብዲሳ ጀማል ላይ የአዳማ ከተማ የአሰልጣኞች ቡድን ከፍ ያለ ዕምነት ነበራቸው። አሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤል በተደጋጋሚ በሚሰጧቸው ድህረ ጨዋታ ቃለመጠይቆች ተጫዋቹ ከጉዳት ሙሉ ለሙሉ በሚያገግምበት ወቅት ለቡድኑ የተሻለ አበርክቶ እንዲሚኖረው ሲደመጡ ተስተውሏል። ታድያ ይህ ቃላቸው በዚህ ሳምንት ፍሬ አፍርቶ ቡድኑ ሀዋሳ ከተማን ሲረታ አብዲሳ ጀማል ሐት-ትሪክ መስራት ችሏል።

በውድድር ዘመኑ ሐት-ትሪክ መስራት የቻለው አራተኛ ተጫዋች መሆን የቻለውና ሁሉንም በክፍት ጨዋታ የማስቆጠር ብቸኛ የሆነው አብዲሳ ጀማል ጥሩ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ አጥቂ መሆኑን አስመስክሯል። ያስቆጠራቸው ሦስቱም ግቦች በአስደናቂ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ የተገኙ ሲሆን ተጫዋቹም ሒደቶቹን ወደ ግብነት የቀየረበት መንገድ አስደናቂ ነበር።

አጥቂው ከጨዋታው በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት ” አውቅ ነበር ከፍተው እንደሚሄዱ፤ አስቤበትም ነው የገባሁት። የመስመር ተከላካዮቹ ነቅለው እንደሚሄዱ ስለተነገረን እና ሁለት የመሐል ተከላካዮች ብቻ ስለሚቀሩ እነርሱን እንደማልፋቸው እርግጠኛ ነበርኩኝ። እኔም አቅሜን ሰብስቤ በመጠቀም ሐት ትሪክ ልሰራ ችያለው።” ብሏል።

አዳማ ከተማ ካስቆጠራቸው ግቦች ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን ግቦች በሁለት ጨዋታዎች ማስቆጠር የቻለው አጥቂው በአምስት ግቦች የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ፉክክር ውስጥ መግባት ችሏል።

👉ያኔም አሁንም ያው ደጉ ደበበ

ከ1994 አንስቶ በከፍተኛ ደረጃ እግርኳስን በመጫወት ላይ የሚገኘው እና ለብዙ እግርኳሰኞች በአርዓያነት መጠቀስ የሚችለው ደጉ ደበበ በ20ኛው የውድድር ዘመኑ የመጀመሪያዋን ግብ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ጅማ አባጅፋር ላይ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሯል።

በ2010 በአምበልነት ብዙ ክብሮች ከተቀዳጀበት ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲለቅ የእግርኳስ ህይወቱ ያበቃ መስሎ ቢታይም በወላይታ ድቻ ቤት ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቃቱን ጠብቆ በሚገባ ቡድኑን እያገለገለ ይገኛል። በአመዛኙ ወጣት በሆኑ ተጫዋቾች በተገነባው የድቻ ቡድን ውስጥ ከጥሩ ተከላካይነቱ ባሻገር በአምበልነት ቡድኑን እየመራ ከፊታቸው ብዙ ለሚጠብቃቸው የቡድን አጋሮቹ ተምሳሌትነቱን እያሳየ የሚገኘው ደጉ በዚህ ሳምንት በጅማው ጨዋታ ለቡድኑ ቀዳሚውን ግብ በማስቆጠር በሩን ከፍቷል።

👉ባለ ብዙ መልኩ መሳይ አገኘሁ

ወላይታ ድቻ ዘንድሮ ፈታኝ የውድድር ዘመን እያሴለፉ ከሚገኙ ክለቦች አንዱ ቢሆንም ወጣት ተጫዋቾችን በመጠቀም ረገድ ምሳሌ ከሆኑ ጥቂት ክለቦች አንዱ መሆኑን ቀጥሏል። በሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ ቡድኑ ጅማ አባ ጅፋርን 3-1 ሲረታ በአማካይ ቦታ ተሰልፎ ምርጥ ቀን ያሳለፈው ወጣቱ መሳይ አገኘሁም ለዚህ በምሳሌነት የሚቀርብ ነው።

ከወጣት ቡድኑ ያደገው የመስመር ተጫዋቹ ዘንድሮ በሊጉ የመጀመርያዎቹ ጨዋታዎች ላይ በግራ መስመር ተከላካይ ስፍራ ላይ ተጫውቶ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ያሳየ ሲሆን በትናንቱ ጨዋታ ደግሞ በአምስት አማካዮች በተዋቀረው የድቻ የመሐል ክፍል የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲመራ ውሏል። ቡድኑ የአቻነት ግብ ባስተናገደ ቅፅበት ወደመሪነት እንዲመለስ ያስቻለች ጎል ያስቆጠረው መሳይ ከማዕዘን ምት የተቆጠሩትን ሁለቱንም ውጤታማ ኳሶች ለደጉ እና አንተነህ አመቻችቷል። ተጫዋቹ ከሁለገብነቱ ባሻገር የቆመ ኳሶችን የሚያደርስበት መንገድ ድንቅ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ