ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ10ኛ ሳምንት ምርጥ 11

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ ላቅ ያለ ብቃት ያሳዩ  እና ሙሉ ለሙሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በምርጥ 11 ውስጥ የተካተተቱ ተጫዋቾችን መርጠናል።

አሰላለፍ : 3-5-2

ግብ ጠባቂ

ምንተስኖት ዓሎ – ሰበታ ከተማ

ለመጀመሪያ ጊዜ ተከታታይ ጨዋታዎችን የመሰለፍ ዕድል ያገኘው ምንተስኖት ቡድኑ ባሳለፍነው ሳምንት በሲዳማ ሲሸነፍ ጥሩ እንቅስቃሴ አድርጎ በተጠባባቂነት ይዘነው ነበር። በዚህ ሳምንት ደግሞ በሆሳዕናው ጨዋታ በአወዛጋቢ የዳኝነት ውሳኔ የተሰጠው የዳዋ ሆቴሳን ፍፁም ቅጣት ምት አድኖ ቡድኑ ዳግም በዳኞች ውሳኔ ነጥብ እንዳያጣ አድርጓል።

ተከላካዮች

ትዕግስቱ አበራ – አዳማ ከተማ

ከደስታ ጊቻሞ ጋር በሁሉም የአዳማ ጨዋታዎች ላይ ተጣምሮ ያየነው ትዕግስቱ ጥሩ የጨዋታ ቀንን አሳልፏል። ፈጣኖቹ እነ መስፍን ታፈሰን ከመቆጣጠር ባለፈ የአየር ላይ ኳሶችን በማውጣት እና ኳስ በማራቅ ቡድኑ የሀዋሳን ጥቃት አቅም ሲያሳጣ ወሳኝ ሚና ኖሮት ተመልክተነዋል።

ደጉ ደበበ – ወላይታ ድቻ

አንጋፋው የመሐል ተከላካይ የቡድኑን የኋላ መስመር በአግባቡ ሲመራ ቆይቶ ዛሬም ጠንካራ አቋሙን በማሳየቱ ቀጥሎበታል። የወትሮው ቡድን የመምራት ክህሎቱን ባሳየበት የጅማ አባ ጅፋሩ ጨዋታ ቡድኑ በሳጥን ውስጥ ደጋግሞ ዕድሎችን እያባከነ በቆየበት ጊዜ የማጥቃት መንፈሱ ከመዳከሙ በፊት ወሳኝ የሆነችውን አስደናቂ የግንባር ኳስ ማስቆጠር ችሏል።

ሰንደይ ሙቱኩ – ሲዳማ ቡና

በተለዋዋጩ የሲዳማ የኃላ ክፍል ውስጥ አልፎ አልፎ ዕድሎችን ሲያገኝ የነበረው ኬኒያዊው ተከላካይ ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ ተመልሶ መልካም እንቅስቃሴ አድርጓል። ቡድኑ ቅዱስ ጊዮርጊስን በገጠመበት ጨዋታ በተገበረው የሰው በሰው የመከላከል ዕቅድ ውስጥ ጌታነህ ከበደን በአግባቡ በመቆጣጠር ሲዳማ ግብ እንዳይቆጠርበት የበኩሉን አድርጓል።

አማካዮች

በላይ ዓባይነህ – አዳማ ከተማ

አዳማ በቀኝ መስመር አጥቂነት የተጠቀመው በላይ አባይነህን በጨዋታው ከማጥቃት በተጨማሪ በነበረው የመከላከል ትጋት ለዛሬ በመረጥነው አደራደር ውስጥ የቀኝ መስመር ተመላላሽነት ሚና ሰጥተነዋል። እንደ ቡድኑ ሁሉ ከወትሮው የተለየ ንቃት ላይ የነበረው በላይ አንድ ጎል የሆነ ኳስ ሲያቀብል አስፈሪ በነበረው የአዳማ መልሶ ማጥቃት ሒደት ውስጥ የቡድኑ የቀኝ ወገን ለነበረው ጥንካሬ ወሳኝ ሚና ተወጥቷል።

ደሳለኝ ደባሽ – አዳማ ከተማ

በአዳማ አሰላለፍ ውስጥ አዘውትሮ የማይጠፋው ደሳለኝ ብዙ የተባለለትን የሀዋሳ ከተማን የአማካይ ክፍል እንቅስቃሴ ፍሬ እንዳያፈራ የተሰጠውን ሚና በአግባቡ ሲወጣ ውሏል። አዳማ በተከተለው የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ውስጥም ሁለተኛው ግብ ሲቆጠር ጥቃቱን ፈጥኖ ከመሐል ያስጀመረው ደሳለኝ ነበር።

መሳይ አገኘሁ – ወላይታ ድቻ

ዘንድሮ በመስመር ተከላካይነት ሲጫወት ከቆየበት ሚና እና ከመጀመሪያ አሰላለፍ ርቆ የነበረው መሳይ ዳግም ተመልሶ የጨዋታው ዋነኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ በመሆን ዕድሉን በአግባቡ ተጠቅሟል። ወጣቱ አማካይ የደጉ ደበበ እና አንተነህ ጉግሳን ግቦች ከማዕዘን በማሻማት አቀባይ ሲሆን ድቻን ከዕረፍት በፊት ወደመሪነት የመለሰችውን ወሳኝ ጎልም ራሱ ከመረብ አገናኝቷል።

ቴዎድሮስ ገብረእግዚአብሄር – አዳማ ከተማ

በምርጫችን ውስጥ ለመካተት ከወልቂጤው አብዱልከሪም ወርቁ ጋር ተቀራራቢ ፉክክር ያደረገው ቴዎድሮስ ተመራጭ ሆኗል። እምብዛም የመሰለፍ ዕድል ሲሰጠው የማይታየው ቴዎድሮስ ደድንቅ የጨዋታ ቀን በማሳለፍ የቡድኑን ዓይን የከፈተችውን የመጀመሪያ ጎል ሲያቀብል ለሦስተኛው ግብ መገኘት መንስዔ የነበረውን መልሶ ማጥቃትም አስጀምሯል።

ረመዳን የሱፍ – ወልቂጤ ከተማ

የግራ መስመር ተከላካዩ ረመዳን በአንደኛው ሳምንት በተጠባባቂነት ከመረጥነው በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ምርጫችን ውስጥ ተመልሷል። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በተሻጋሪ ኳስ አንድ የጠራ የግብ ዕድል ፈጥሮ የነበረው ረመዳን ከቆይታ በኃላ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመግባት ሱራፌል ጌታቸውን አልፎ ለአሜ መሐመድ ያደረሰው ኳስ ቡድኑን ቀዳሚ ወዳደረገ ጎል ተቀይሮለታል።

አጥቂዎች

አሜ መሐመድ – ወልቂጤ ከተማ

ከመጀመሪያ አሰላለፍ ርቆ የቆየው አሜ መሐመድ የአሳሪ አልመሀዲን ጉዳት ተከትሎ ወደ ሜዳ በገባ በዘጠኝ ደቂቃ ውስጥ ቡድኑን መሪ ያደረገች ጉል አስቆጥሯል። በሁለተኛው አጋማሽም አቡበከር ሳኒ ያስቆጠራትን ኳስ አመቻችቶ ያቀበለው አሜ ነበር። ጨዋታውን በመስመር አጥቂነት ቢያደርግም በመረጥነው አደራደር ውስጥ ፊት መስመር ላይ አስቀምጠነዋል።

አብዲሳ ጀማል – አዳማ ከተማ

ከጉዳት ጋር እየታገለ 10ኛው ሳምንት ላይ የደረሰው አብዲሳ ጀማል ሦስት ግቦችን ከመረብ አሳርፎ በአሰልጣኞቹ ሲጣልበት የነበረውን ተስፋ እውን አድርጎ አዳማን እፎይ አስብሏል። ለመልሶ ማጥቃት ምቹ የሳጥን ውስጥ አጥቂ እንደሆነ ባሳየበት በዚህ ጨዋታ የሀዋሳ ተከላላዮችን ክፍተት በአግባቡ ተጠቅሞ ቦታ አያያዙን በማሳመር ያገኛቸውን ዕድሎች ሳይባክን የዕለቱ እና የሳምንቱ ኮከብ መሆን ችሏል።

አሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤል – አዳማ ከተማ

ከሰባት ተከታታይ ጨዋታዎች በኃላ ወደ ድል በተመለሰው አዳማ ከተማ ስኬታማ ሳምንት ውስጥ አሰልጣኙ ጉልህ ድርሻ ነበራቸው። ከወትሮው በተለየ ጉልበት በፈጣን መልሶ ማጥቃት ለመጫወት እና የሀዋሳን ደካማ ጎን ለመጠቀም የአደረደር እና የአምስት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ይዘውት የገቡት የጨዋታ ዕቅድ ሰምሮላቸው ከጨዋታ ብልጫ ጋር ባለ ድል ሆነዋል።

ተጠባባቂዎች

ፍቅሩ ወዴሳ – ሲዳማ ቡና
ጊት ጋትኮች – ሲዳማ ቡና
ደስታ ጊቻሞ – አዳማ ከተማ
አብዱልከሪም ወርቁ – ወልቂጤ ከተማ
ሚኪያስ መኮንን – ኢትዮጵያ ቡና
ፍፁም ዓለሙ – ባህር ዳር ከተማ
ፀጋዬ ብርሀኑ – ወላይታ ድቻ


© ሶከር ኢትዮጵያ