የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ነገ ዝግጅቱን ይጀምራል

የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የመጨረሻ ሁለት የምድብ ጨዋታቸውን መጋቢት ወር ላይ ከማዳጋስካር እና አይቮሪኮስት ጋር የሚያደርጉት ዋልያዎቹ ነገ ዝግጅታቸውን ይጀምራሉ።

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሊግ ውድድሮች ሳይቋረጡ የብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ማድረግ እንደሚቻል በጅማ በነበረው የአጭር ጊዜ ዝግጅት በማድረግ መልካም ጅማሮ ማድረጋቸው ይታወቃል። የዚህ አካል የሆነው ሁለተኛ ምዕራፍ ዝግጅታቸውን ከቀናት በፊት በጠሩት 28 ተጫዋቾች አማካኝነት ነገ በአዲስ አበባ የሚጀምሩ ይሆናል።

ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች ጠዋት ሪፖርት ካደረጉ በኃላ ከሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም አልያም ሲኤምሲ በሚገኘው የንግድ ባንክ ሜዳ ልምምዳቸውን የሚጀምሩ ይሆናል።

በቀጣይ በባህር ዳር ከተማ የሚካሄደው ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ከ11ኛ እስከ 16ኛው ሳምንት ድረስ ጨዋታዎች እንደተጠናቀቁ የመጨረሻውን ዝግጅታቸውን በዛው ጨዋታውን በሚያደርጉበት ባህር ዳር ከተማ የሚያደርጉ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መጋቢት ወር ላይ ማዳጋስካር እና አይቮሪኮስት በመግጠም ወደ አፍሪካ ዋንጫ የመግባት ዕድላቸውን ይወስናሉ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *