ድሬዳዋ ከተማ ከአሰልጣኙ ጋር ተለያየ

ድሬዳዋ ከተማን በዋና አሰልጣኝ በመሆን ያለፉትን ወራት ቡድኑን እየመሩ የቆዩት አሰልጣኝ ፍስሐ ጥዑመልሳን ቀዛሬው ዕለት ከክለቡ ጋር በስምምነት ተለያዩ።

ከ2010 ጀምሮ ድሬደዋን ምክትል አሰልጣኝ በመሆን ሲሰሩ የቆዩት አሰልጣኝ ፍስሐ ጥዑመልሳን ባሳለፍነው የውድድር ዘመን አሰልጣኝ ስምኦን ዓባይን በመተካት ዋና አሰልጣኝ ሆነው እስከ ዛሬው ዕለት ድረስ ቡድኑን ሲያገለግሉ መቆየታቸው ይታወቃል። ክለቡ በሚፈልገው ደረጃ ውጤት አልመጣም በሚል አስቀድሞ ለአሰልጣኙ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ አድርሷቸው የነበረ ሲሆን ቡድኑን ለቀጣይ ጨዋታ ለማዘጋጀት ባህር ዳር ከተማ ባሉበት ወቅት በክለቡ በኩል ጥሪ ተደርጎላቸው በትናንትናው ዕለት ወደ ድሬዳዋ በመመለስ ዛሬ ከክለቡ አመራሮች ጋር ውይይት ካደረጉ በኃላ በስምምነት ለመለያየት መስማማታቸው ታውቋል። ይህን ተከትሎ በቀጣይም ቀናት ክለቡ አዲስ አሰልጣኝ እንደሚሾም ይጠበቃል።

አሰልጣኝ ፍስሐ በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የማይረሱ ፈገግታን የሚጭሩ አስተያየቶችን ከጨዋታ በፊት እና በኃላ በመስጠት የሊጉ ድምቀት እንደነበሩ ይታወቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ