የአሠልጣኞች አስተያየት | ጅማ አባጅፋር 1-0 ሲዳማ ቡና

በጅማ አባጅፋር አሸናፊነት ከተጠናቀቀው የ4 ሰዓት ጨዋታ በኋላ የቡድኖቹ አሠልጣኞች አስተያየታቸውን ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።

ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ጅማ አባጅፋር

ቡድኑ ስላገኘው የመጀመሪያ ሦስት ነጥብ?

ቡድናችን ዛሬ ሦስት ነጥብ እንዲያገኝ ያስቻሉት ተጫዋቾቻችን ትልቅ ዋጋ ሊሠጣቸው ይገባል። ተጫዋቾቻችን ሜዳ ላይ የነበራቸው ቁርጠኝነት፣ ተነሳሽነት እና ፍላጎት ሦስት ነጥብ እንድንሳካ አድርጎናል። በዚህም ሁሉንም ተጫዋቾች ላመሰግን እወዳለሁ።

በሁለተኛው አጋማሽ ቡድኑ ስለተከተለው የጨዋታ መንገድ?

በሁለተኛው አጋማሽ ጥቅጥቅ ብለን በመከላከል ተጫውተናል። ይህም ከእኔ ብቻ ሳይሆን ተጫዋቾቹ ራሱ ውጤቱን ለማስጠበቅ ካደረጉት የግል ጥረት የመጣ ነው። በአጠቃላይ ግን በጨዋታው በምንፈልገው መንገድ ተጫውተናል ባልልም እንደ መጀመሪያ ጥሩ ነው። ድሉም ለተጫዋቾቻችን ስነልቦና የሚያሚመጣው ነገር ስላለ ጥሩ ነው።

ስለ ቀጣይ ጨዋታዎች?

በቀጣይ የምንሰራቸው ስራዎች አሉ። በተለይ እንደ ቡድን የበላይ ሆነን ጨዋታዎችን የምናረግበት መንገድ ላይ መስራት አለብን። እኔ ጎሎች በእንቅስቃሴዎች ውስጥ ሆነው እንዲገቡ እፈልጋለሁ። አሁን ላይ ያሉን ተጫዋቾች ውስን ናቸው። በጉዳት እና በኮንትራት ችግር አብረውን የማይገኙ ተጫዋቾች አሉ። ስለዚህ ይህንን ነገር አስተካክለን በቀጣይ በሚኖሩን የእረፍት ጊዜያት እንደ ቡድን በደንብ ተጠናክረን እንቀርባለን።

ገብረመድህን ኃይሌ – ሲዳማ ቡና

ስለ ጨዋታው…?

ጨዋታው መጥፎ የሚባል አደለም። እርግጥ መሸነፋችን መጥፎ ሊያደርገው ይችላል። ግን እንደአጨዋወታችን ማሸነፍ ይገባን ነበር። እግርኳስ ጨዋታ በስህተት የተሞላ ነው እና እነሱ ስህተቱን ተጠቅመው ግብ አስቆጥረውብናል። ከግቡም በኋላ በጥብቅ የመከላከል አደረጃጀት ስለሆነ ሲጫወቱ የነበረው በውስኑ አቅማችን ይህንን ማስከፈት አልቻልንም። ወደፊት ግን እነዚህን ነገሮች እያስተካከልን ሄደን ወደምንፈልገው ደረጃ እንደርሳለን ብለን እናስባለን።

ስለ ቡድኑ እንቅስቃሴ…?

ቡድኑን እያየሁት ነው። ገና ቡድኑን በደንብ እስካቀው ድረስ ሀሳብ መስጠት ያስቸግረኛል። ከዛሬው ጨዋታ በፊትም ለአራት ቀን ያህል ብቻ ነው ልምምድ የሰራነው። በአራት ቀን ልምምድ ለውጥ ማምጣትም ትንሽ ይከብዳል። ምንም ቢሆን ምንም ግን የዛሬው ጨዋታ ትምህርት ይሆነናል። የምንፈልገውን ቡድን ለመገንባት ግን ጊዜ ያስፈልገናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ