ሪፖርት | ዐፄዎቹ መሪነታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል

የ12ኛ ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ መርሐ-ግብር የሆነው የሀዋሳ ከተማ እና የፋሲል ከነማ ጨዋታ በዐፄዎቹ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በአሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት የሚመሩት ሀዋሳ ከተማዎች በ11ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር ከወልቂጤ ከተማ ጋር አቻ ከተለያዩበት ቋሚ 11 አለልኝ አዘነ እና ዩሃንስ ሴጌቦን በወንድማገኝ ኃይሉ እና ዘነበ ከድር ቀይረው ወደ ሜዳ ገብተዋል። የሊጉ መሪ የሆኑት ፋሲል ከነማዎች በበኩላቸው በድሬዳዋው ጨዋታ ከተጠቀሙበት አሰላለፍ አንድ ተጫዋች ብቻ ለውጠው ለጨዋታው ቀርበዋል። በዚህም ይሁን እንዳሻውን ከቅጣት በተመለሰው ሱራፌል ዳኛቸውን ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ኳስን ተቆጣጥረው የጨዋታውን የመጀመሪያ ደቂቃ መጫወት የጀመሩት ፋሲል ከነማዎች ገና ጨዋታው ሩብ ሰዓት ሳያስቆጥር መሪ ሆነዋል። በ11ኛው ደቂቃም ከመሐል በረጅሙ ወደ ቀኝ መስመር የተላከውን ኳስ በሚገባ የተቆጣጠረው ሽመክት ጉግሳ ያገኘውን ኳስ በጥሩ አቋቋም ላይ ለነበረው በረከት ደስታ አቀብሎት በረከት ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። ገና በጊዜ መሪ የሆኑት ፋሲሎች ግቡን ካስቆጠሩ ከአራት ደቂቃዎች በኋላም በጥሩ አንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሀዋሳዎች የግብ ክልል ደርሰው ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር።

ገና ከጅማሮው ጥቃቶች የበዛባቸው ሀዋሳ ከተማዎች በ18ኛው ደቂቃ ያገኙትን የቅጣት ምት በአለልኝ አዘነ አማካኝነት ወደ ግብ መትተውት በቶሎ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ሞክረው ከሽፎባቸዋል። በተጨማሪም በ26ኛው ደቂቃ አማካዩ ኤፍሬም ዘካሪያስ ከርቀት ወደ ግብ በመታው ነገርግን ሳማኪ በተቆጣጠረው አጋጣሚ የፋሲልን የግብ ክልል ጎብኝተው ተመልሰዋል።

በርከት ያሉ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ወደ ሜዳ ያስገቡት ፋሲል ከነማዎች አጋማሹ ሊጠናቀቅ 5 ደቂቃዎች ሲቀሩት ግቡ ሲቆጠር አመቻችቶ ባቀበለው ሽመክት ጉግሳ የግብ እድል ፈጠራ በመጠቀም መሪነታቸውን ለማስፋት ተቃርበዋል። ፋሲሎች ይህንን ሙከራ ባደረጉ በደቂቃዎች ልዩነት ለተሰነዘረባቸው ጥቃት ምላሽ ለመስጠት ያሰቡ የሚመስሉት ሀዋሳዎች በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ፋሲል ግብ ክልል ደርሰው በመስፍን ታፈሰ አማካኝነት ሙከራ ሰንዝረዋል።

የሀዋሳ ተከላካዮችን ስራ አብዝተው የታዩት የፋሲል ከነማ ተጫዋቾች በ44ኛው ደቂቃ መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ አድርገዋል። በዚህ ደቂቃም የግራ መስመር ተከላካዩ አምሳሉ ጥላሁን ከሱራፌል ዳኛቸው የተቀበለውን ኳስ በሚገርም ሁኔታ ከርቀት በመምታት የሜንሳህ ሶሆሆ መረብ ላይ አሳርፎታል። ወደ ጨዋታው በቶሎ ለመመለስ ሲታትሩ የነበሩት ሀዋሳዎች በመጀመሪያዎቹ እና በመጨረሻዎቹ የአጋማሹ ደቂቃዎች በተቆጠረባቸው ጎሎች እየተመሩ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻሻለ መነሳሳት ይህንን አርባ አምስት የጀመሩት ሀዋሳ ከተማዎች በፈጣኖቹ አጥቂዎቻቸው በመታገዝ ከጨዋታው ነጥብ ይዞ ለመውጣት ታትረዋል። በተቃራኒው መሪነታቸውን አስፍተው ወደ መልበሻ ክፍል አምርተው የነበረው ፋሲሎች በነፃነት ኳስን በመቆጣጠር አጋማሹን ጀምረዋል።

ያለፉትን ሦስት ጨዋታዎች ተሸንፈው የዛሬውን ጨዋታ የጀመሩት ሀዋሳዎች በ68ኛው ደቂቃ በመስፍን አማካኝነት ጥሩ ሙከራ አድርገዋል። ይህንን ሙከራ ካደረጉ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ዳግም በቀኝ መስመር ወደ ፋሲል የግብ ክልል በመድረስ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል። በዚህ ደቂቃም ፈጣኑ ተጫዋች ኤፍሬም አሻሞ በጥሩ ቅልጥፍና ከመስመር ወደ ሳጥን ይዞ የገባውን ኳስ ተቀይሮ ወደ ሜዳ ለገባው ወንድማገኝ ኃይሉ አቀብሎት ወንድማገኝ ግብ አስቆጥሯል።

ወንድማገኝ ባስቆጠረው ጎል እጅግ የተነቃቁት ሀዋሳዎች የአቻነት ጎል ፍለጋቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል። በዚህም በ74ኛው ደቂቃ በግራ መስመር ተከላካዩ ዩሃንስ ሰገቦ አማካኝነት ጥሩ የግብ ማግባት ዕድል ፈጥረው ነበር። የሀዋሳዎችን የግብ ማግባት ፍላጎት ተከትሎ ከተከላካይ ጀርባ ሰፊ የማጥቂያ ቦታ ያገኙት ፋሲሎች ከመከላከል ወደ ማጥቃት በተደረገ ሽግግር አማካኝነት የተገኘን ዕድል ሱራፌል ለሙጂብ አቀብሎት የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ጥሩ ጥቃት ፈፅሟል። በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ መነቃቃት የታየባቸው ሀዋሳዎች ከጨዋታው ነጥብ ይዞ ለመውጣት ቢጥሩም ሳይሳካላቸው ጨዋታው በፋሲል ከነማ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ በጨዋታው ሦስት ነጥብ ያገኙት ፋሲል ከነማዎች ሁለተኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው ኢትዮጵያ ቡና ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሰባት በማሳደግ መሪነታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል። በተቃራኒው ሽንፈት ያስተናገዱት ሀዋሳዎች በበኩላቸው በሰበሰቡት 15 ነጥቦች ያሉበት 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ