ቅዱስ ጊዮርጊስ በሳላዲን ሰዒድ ላይ ውሳኔ አሳለፈ

ከሳምንታት በፊት በሳላዲን ሰዒድ ላይ ገደብ ጥሎ የቆየው ቅዱስ ጊዮርጊስ ውሳኔ አሳልፏል።

ክለቡ ሳላዲን በግርድፉ የዲስፕሊን ግድፈት ስለመፈፀሙ በመግለፅ ከሳምንታት በፊት “ከዋናው ቡድን ጋር ለተጨማሪ ጊዜ አብሮ እንዲቆይ መፍቀድ በውድድሩ ላይ እየተፋለመ ለሚገኘው ቡድናችን ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ስለሚያመዝን ከቡድን መሪው በሥነ ምግባር ዙሪያ በዝርዝር በሚቀርበው ሪፖርት ላይ በቦርዱ ውሳኔ እስከሚገኝ ድረስ ከተስፋ ቡድን ጋር ልምምዱን እያደረገ እንዲቆይ” የሚል መመርያ መስጠቱን ማሳወቁ ይታወቃል።

የካቲት አራት ቀን መደበኛ ስብሰባውን ያደረገው የክለቡ የቦርድ አመራር ቡድን መሪው የቀረበውን ሪፖርት ከተመለከተ በኋላ በሳላዲን ሰዒድ ጉዳይ ዙርያ ውሳኔ አሳልፏል። በውሳኔውም እገዳ ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ እስከ መጋቢት 10 ድረስ ከዋናው ቡድን እንቅስቃሴ እንዲታገድ፣ የአምስት ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እና እስከ መጋቢት 10 ድረስ ከተስፋ ቡድን ጋር አብሮ እንዲሰራ ውሳኔ ተላልፎበታል።


© ሶከር ኢትዮጵያ