አዳማ ከተማ አዲስ አሰልጣኝ ሾሟል

የአዳማ ከተማ ቦርድ ሁለት አሰልጣኞችን ጠርቶ ካነጋገረ በኋላ በዛሬው ዕለት ዋና አሰልጣኝ መሾሙን ሶከር ኢትዮጵያ በስፍራው በመገኘት አረጋግጣለች።

በኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ደካማ የውድድር አመትን እያሳለፈ የሚገኘው አዳማ ከተማ የመጀመሪያውን ዙር የሊጉን ጨዋታዎች ያጠናቀቀ ሲሆን በኢትዮጵያ ቡና በባህርዳር ስታዲየም 4ለ1 በመጨረሻ የዙሩ ጨዋታ ከተረታ በኃላ ክለቡን በዋና አሰልጣኝነት ሲመሩ ከነበሩት አስቻለው ኃይለሚካኤል ጋር መለያየቱ ይታወሳል፡፡ የአሰልጣኙን ከኃላፊነት መነሳት ተከትሎ የአዳማ ከተማ ቦርድ ሁለት አሰልጣኞች የክለቡ ፅህፈት ቤት ከማክሰኞ ጀምሮ ጠርቶ ሲያነጋግር ቆይቷል፡፡ ከሀዋሳ ከተማ ጋር በተሰረዘው የውድድር ዓመት የተለያዩት አሰልጣኝ አዲሴ ካሳ እና ከሳምንታት በፊት ከሲዳማ ቡና ጋር የተለያዩት አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉን በተለያዩ ጉዳዮች ዙርያ ካናገረ በኃላ አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉን ምርጫው አድርጓል፡፡ ትናንት በክለቡ የበላይነት አካላት ተደውሎላቸው አዳማ የመጡት አሰልጣኝ ዘርአይም በዛሬው ዕለት አዳማን ለአንድ ዓመት ለማሰልጠን ተስማምተዋል፡፡

በሀዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ቡና በተጫዋችነት ያሳለፉት አሰልጣኙ ወደ አሰልጣኝነት ህይወት በ2009 በመግባት ከ20 ዓመት በታች የክለቡ አሰልጣኝ ሆኖ አገልግሏል፡፡ 2010 ላይ ደግሞ የአሰልጣኝ ዓለማየሁ ዓባይነህ ረዳት በመሆን በሲዳማ ቡና የአሰልጣኝነት ህይወቱን የመራ ሲሆን በ2010 የአሰልጣኙን መሰናበት ተከትሎ በዋና አሰልጣኝነት እስከ ዘንድሮ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ በክለቡ ውስጥ ቆይታን አድርገዋል፡፡ 2011 ሲዳማ ቡና መቐለ 70 እንደርታን ተከትሎ በፕሪምየር ሊጉ ሁለተኛ ደረጃን እንዲይዝ የረዱት አሰልጣኙ በውጤት መጥፋት የተነሳ ከሲዳማ ቡና ጋር መለያየታቸው ይታወቃል፡፡

የክለቡ የበላይ አካላት አሰልጣኙ ክለቡን በሊጉ እንዲያቆዩ በዋናነት የሰጣቸው የቤት ስራ ሲሆን አሰልጣኙም ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ጠንካራ ተፎካካሪ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን የነገሩን ሲሆን አዳዲስ ለቡድኑ ይመጥናሉ የሚባሉ ተጫዋቾች ወደ ክለቡ በማምጣት በክለቡ ብዙም ግልጋሎት ያልሰጡ ተጫዋቾችን ለመሸኘት በተጨማሪም አዲስ ረዳት አሰልጣኝ ወደ ክለቡ የማምጣት ፍላጎት እንዳላቸው አሰልጣኝ ዘርዓይ ገልፀዋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ