ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

የሳምንቱን ዐበይት ጉዳዮች የምንዘጋው እንደተለመደው በሌሎች ጉዳዮች ላይ በምናተኩርበት ፅሁፍ ይሆናል።

👉 ድንቅ ቀን ያሳለፉት ረዳት ዳኞች

በዚህ የውድድር ዘመን ጨዋታዎች በሱፐር ስፖርት መተላለፋቸውን ተከትሎ የብዙሀኑ ትኩረት ማዕከል ከሆኑ ጉዳዮች መካከል የዳኝነት ስህተቶች ናቸው። በተለይም የትክክለኛ ጎሎች መሻር ፣ የጨዋታ ውጪ ጎሎች መፅደቅ ፣ ከፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔዎች ላይ የረዳት ዳኞች ድክመት በተደጋጋሚ ሲነሳ ተስተውሏል። በንፅፅር የተሻለ ዳኝነት በተስተዋለበት በዚህ ሳምንት ግን በተለይ የሀዲያ ሆሳዕና እና ጅማ አባ ጅፋር ጨዋታን የመሩት ቢኒያም ወርቃገኘሁ እንዲሁም ረዳት የነበሩት ኤልያስ አበበ እና እሱባለው መብራቱ የነበራቸው ብቃት ግሩም ነበር።

በተለይም የረዳት ዳኞቹ እያንዳንዱ የጨዋታ ውጪ ውሳኔያቸው በምስል ምልሰት ሲታዩ በትክክል የተወሰኑ ሲሆኑ በአንድ አጋጣሚ ቢስማርክ አፒያ በወንድማገኝ ማርቆስ ላይ በተሰራው ጥፋት የመሐል ዳኛው የፍፁም ቅጣት ምት ለመስጠት ቢወስኑም እሱባለው መብራቱ ቢስማርክ አስቀድሞ ከጨዋታ ውጪ ነው በማለታቸው ለውዝግብ መነሻ ሊሆን የነበረው ፍፁም ቅጣት ምት ሳይመታ ቀርቷል። በዚህ መልኩ መናበብ የሚታይባቸው የዳኝነት ውሳኔዎች ውድድሩን ከውዝግብ ከማጥራት ባለፈ የዳኞችን ጠንካራ ጎንም የሚያመለክቱ በመሆናቸው ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል እንላለን።

👉 በቁጥር የተመናመኑ ተጠባባቂ ተጨዋቾች

በዘንድሮው የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቡድኖች በቀዳሚ አሰላለፋቸው ውስጥ ከሚጠቀሟቸው ተጨዋቾች ውጪ ህጉ በሚፈቅደው መሰረት 12 የሚሆኑ ተጠባባቂ ተጨዋቾችን ይዘው ሲገቡ ይታያል። ይህም ለሚፈጠርባቸው ከጉዳት ጋር የተያያዘ ለውጥ አልያም የቡድናቸው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ከማስተካከል አንፃር አሰልጣኞች ለሚያደርጓቸው ቅያሪዎች ሰፊ አማራጭ የመስጠቱ ጉዳይ በግልፅ የሚታይ ሆኖ ቆይቷል።

አሁን አሁን ግን በጉዳት መበራከት ፣ በኮቪድ እና በሌሎች ጉዳዮች መነሻነት የተጠባባቂ ተጨዋቾች ቁጥር ሲቀንስ ይስተዋላል። በዚህ ሳምንትም በተለይ ሀዲያ ሆሳዕና እና ወላይታ ድቻ ከሁለት ግብ ጠባቂዎች ውጪ ሦስት እና አራት የሜዳ ላይ ተጫዋቾችን ብቻ በተጠባባቂነት በመያዝ ጨዋታቸውን እንዲጀምሩ ተገደው ነበር። ነገር ግን አጋጣሚ ሆኖ በአስገዳጅ ቅያሪዎች አለመፈተናቸው ብቻ ሳይሆን ጨዋታዎቻቸውን በድል መጨረሳቸው ይህ ችግራቸው ጎልቶ እንዳይወጣ አድርጎታል። ክስተቱ አሰልጣኞቹ እና የቡድን አባላቱን የሚያስመሰግን ሲሆን በቀጣይ ግን ክለቦቹ ማስተካከያ ካላደረጉ ውጤት እንዲያጡ ምክንያት ሊሆናቸው እንደሚችል ግልፅ ነው።

👉 ኮቪድ ዳኞችንም እየጎበኘ ይገኛል

የዘንድሮው የውድድር ዓመት በርካታ ለውጦችን እንዲያደርግ ካስገደዱ ምክንያቶች ውስጥ ዋነኛው የኮቪድ 19 ወረርሺኝ መሆኑ ይታወቃል። የቫይረሱ በቀላሉ ተዛማች የመሆኑ ጉዳይ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑት ተጫዋቾችን በአመዛኙ ሲያጠቃ ሰንብቷል። በዚህም ሳቢያ በርካታ ክለቦች ወሳኝ ተጨዋቾቻቸውን እንዳይጠቀሙ ዕክል ሆኖባቸው ቆይቷል።

ይህ የቫይረሱ መጥፎ ተፅዕኖ አሁን ደግሞ ወደ ዳኞች ፊቱን ያዞረ ይመስላል። ስም መግለፁ አስፈላጊ ባይሆንም ባህር ዳር ላይ እየተከናወነ በሚገኘው ውድድር ሁለት አርቢትሮች በቫይረሱ እንደተጠቁ ማወቅ ችለናል። ከሁለቱ አንደኛው አገግመው በዚህ ሳምንት አንድ ጨዋታ መምራት የቻሉ ሲሆን አንደኛው አርቢትር ግን ወደ ሥራቸው ከመመለሳቸው በፊት ከህመሙ እስኪያገግሙ እየተጠበቀ መሆኑን ማወቅ ችለናል።

👉 ብቸኛዋ ሴት ኮሚሽነር በባህር ዳር

በዘንድሮው የቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እያሳየን ከሚገኙ በርካታ አዳዲስ ነገሮች መካከል የሴት ኮሚሽነሮች ተሳትፎ አንዱ ነው። ከዚህ ቀድም ጅማ ላይ በነበረው ውድድር የሲስተር ሣራ ሰዒድን የኮሚሽነርነት ሚና ማንሳታችንም ይታወሳል። ባህር ዳር ላይ እየተደረገ በሚገኘው የውድድሩ ክፍል ደግሞ ኮሚሽነር ተስፋነሽ ተገኔን እያስመለከተን ይገኛል።

የቀድሞዋ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተስፋነሽ ተገኔ በ12ኛው ሳምንት ጅማ አባ ጅፋር ከ ሲዳማ ቡና 13ኛው ሳምንት ላይ ደግሞ ሀዲያ ሆሳዕና ከጅማ አባ ጅፋር ያደረጉትን ጨዋታዎች በኮሚሽነርነት መምራት ችለዋል።

በእስካሁኑ የሊጉ ጉዞ ካሉት ሦስት ሴት ኮሚሽነሮች ውስጥ ሁለቱ ኃላፊነት ላይ ሆነው የታዩ ሲሆን በቀጣይ ደግሞ ሌላኛዋን ሴት ኮሚሽነር ሠርካለም ከበደን እንደምንመለከታቸው ይጠበቃል።

👉 የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች አለመታደም

የዘንድሮው የውድድር ፎርማት ከሚያገኛቸው ጥቅሞች አንዱ ያለ እንግልት የተጨዋቾችን አቋም አንድ ቦታ ላይ ሆኖ መገምገም ማስቻሉ ነው። በዚህ ረገድ ውድድሩ ከተጋጣሚ አሰልጣኞች በተጨማሪ ለብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኞች ትልቅ ግብዐት እንደሆነ ይታመናል።

ነገር ግን አዲስ አበባ ላይ የነበረው በብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኞች ዘንድ በአካል ተገኝቶ ጨዋታዎችን የመመልከቱ ነገር በዛው እንደተገታ ቀርቷል። እርግጥ ነው ጨዋታዎች የቴሌቪዢን የቀጥታ ስርጭት ሽፋን ማግኘታቸው ለአሰልጣኞቹ ትልቅ እገዛ ይኖረዋል። ያም ቢሆን ከኳስ ውጪ የሚኖሩ እንቅስቃሴዎችንም ሆነ የልምምድ መርሐ ግብሮችን ለመከታተል ብሎም ከክለብ አሰልጣኞች ጋር በቅርበት ለመስራት የዋልያዎቹ አሰልጣኞች በውድድር ቦታዎች ላይ መገኘት ለሥራቸው መቃናት የጎላ ድርሻ ይኖረዋል። ይህ ነጥብ በፌዴሬሽኑ በኩል ትኩረት ተሰጥቶት አስፈላጊው ነገር ተሟልቶ አሰልጣኞቹ በውድድሩ መከናወኛ ቦታ ላይ ቢገኙ መልካም እንደሆነ ማንሳት እንወዳለን።

👉 አንደኛው ዙር ሲጠቃለል

የ2013 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር የመጀመሪያው ዙር በያዝነው ሳምንት ተጠናቋል። ከወትሮው የተለየ ገፅታን የተላበሰው ውድድሩ ለ13 የጨዋታ ሳምንታት በዘለቀው የመጀመሪያ ዙር ቆይታው በርከት ያሉ ሁነቶችን አስመልክቶናል።

ከሊጉ መጀመር በፊት በብዙዎች ለሊጉ ክብር ይፎካከራሉ የተባሉት ፋሲል ከነማ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ውድድሩን ከአናት ሆነው ሲመሩ በብዙዎች በሊጉ ለመፎካከር ይቸገራሉ ተብለው ቅድመ ግምት ያገኙት አዳማ ከተማ እና ጅማ አባጅፋር በሊጉ ግርጌ ተቀምጠዋል። በተቃራኒው ለዋንጫ ተፎካካሪነት ይጠበቅ የነበረው ሲዳማ ቡና ሳይጠበቅ የመጀመሪያውን ዙር በ11ኛ ደረጃ ሲያጠናቅቅ እንደ አዲስ የተደራጀው ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ በአዲስ ገፅታ ወደ ዋንጫው ፉክክር የተቀላቀለ ቡድን ሆኗል።

በሊጉ የመጀመሪያ ሳምንታት አካባቢ በርካታ ግቦችን ያስተናግድ የነበረው ውድድሩ በተለይ ውድድሩ ወደ ጅማ ካቀና ወዲህ የሚቆጠሩት ግቦች መጠን ቀስ በቀስ እየቀነሰ ቢመጣም በጥቅሉ ግን ጥሩ ፉክክር የታየበት የውድድር አጋማሽን ተመልከትናል።

ሊጉ በተለምዶ የአንደኛ ዙር እንደተጠናቀቀ ከቀናት እስከ አንድ ወር ድረስ እረፍት መስጠት የተለመደ ቢሆንም ዘንድሮ እየተካሄደ ከሚገኝበት የውድድር ቅርፅ አንፃር ያለ እረፍት ወደ ሁለተኛው ዙር ጨዋታዎች ይሸጋገራሉ። ይህቁንም ከሦስት የጨዋታ ሳምንት በኋላ የባህር ዳር ቆይታ ሲጠናቀቅ እረፍት እንዲኖር መወሰኑ የዘንድሮውን ለየት ያደርገዋል።

ከአስራ ሁለት ዓመታት በኋላ የሊጉ የስያሜ መብት መሸጡ፣ ከሁለት ጨዋታዎች በቀር ሁሉም ጨዋታዎች በሱፐር ስፖርት መተላለፋቸው፣ ውድድር ተከናወነ ለማለት ያህል ብቻ ሲካሄድ የቆየው ሊግ በአንፃራዊነት በተደራጀ መልኩ መካሄዱ እና የመሳሰሉት የአንደኛው ዙር ብሎም የውድድር ዓመቱ ልዩ መገለጫዎች ናቸው።


© ሶከር ኢትዮጵያ