የአሰልጣኞች አስተያየት | ሰበታ ከተማ 2-1 ሀዋሳ ከተማ

የ15ኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመክፈቻ ጨዋታ ሰበታ ከተማ ሀዋሳን 2-1 መርታት ችሏል። ከጨዋታ መጠናቀቅ በኃላም የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።

አብርሃም መብራቱ – ሰበታ ከተማ

በሁለቱ አጋማሽ የተለያየው መልክ ስለነበረው ጨዋታ

“እንዳልከው ሁለቱ አጋማሾች የተለያዩ ነበሩ። በመጀመሪያው አጋማሽ ኳሱን ተቆጣጥረን የተጋጣሚ ተጫዋቾችን ከራሳችን ሜዳ አስወጥተው ብዙ የበላይነት ነበረን፤ ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር የነበረንን የበላይነት ለማስጠበቅ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ የእኛ ተጫዋቾች ወደ ኃላ አፈግፍገዋል። ይህ ደግሞ በእራሳችን ላይ መጠቃትን አስከትሏል ይሄም በፍፁም መታረም እንደሚገባው ተመልክተናል። ከዚህ በተረፈ ግን እንደአጠቃላይ ከጨዋታ ብልጫ ጋር የሚገባንን ነጥብ ማግኘት የቻልንበት ነበር።

ዳዊት እስጢፋኖስ እና አዲሱ የተከላካይ አማካይነት ሚናው

“ዳዊት ያው ያለው ልምድ የሚታወቅ ነው ፤ ያለው የኳስ ክህሎት ጥሩ ነው ምንም እንኳን እዛ ቦታ ላይ ለረጅም ጊዜ ባይጫወትም ያለው ልምድ ግን እዛ ቦታ ላይ ኳስን ተቆጣጥሮ የእኛን ተከላካዮችን ኳስ እያስነካ እንዲወጣና ጨዋታውን አምብቦ እንዲጫወት ነው የምንፈልገው። ከዛም በላይ ደግሞ ወጣት የሆኑት ከፊት ያሉትን ተጫዋቾች እንዲመራልን ብለን ነው ፤ ከዚህ አንፃር በቦታው ላይ ዳዊት ትልቅ ጥቅም እየሰጠን ነው።”

መሉጌታ ምህረት – ሀዋሳ ከተማ

በሁለቱ አጋማሽ የተለያየ መልክ ስለነበረው ቡድኑ

“በእርግጥ ጨዋታው ከባድ ነው ያው ሰበታ ከተማ ኳሱን ይዞ ስለሚጫወት መሀሉን በመጀመሪያው 45 መልቀቅ አልፈለግንም ነበር ነገርግን በጥቃቅን ስህተት ጎሎች ሲቆጠርብን ግዴታ ጎሎች ያስፈልገን ስለነበር አጥቅተን ለመጫወት የፎርሜሽን ለውጦችን አድርገን ተጫውተናል።”

ሁለተኛ ግብ ካስተናገዱ በኃላ በርካታ እድሎችን ፈጥረው ስላለመጠቀማቸው

“በእርግጥ ብዙ እድሎችን ፈጥረናል የአጨራረስ ችግሮች ናቸው ፤ አሁንም አጨራረሳችን ላይ መስራት ይጠበቅብናል። እንቅስቃሴውም ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ ነበር ያው አንዳንድ ጊዜ እንደዚህ አይነት ጨዋታዎች ያጋጥሟሉ ቢሆንም ግን አቻ ውጤት ይገባን ነበር ቢሆን ያው እግርኳስ ስለሆነ እንቀበላለን።አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሜዳ ላይ የሚታየው ነገር ሰአቶች በብዙ ምክንያቶች ይባክናሉ በዚህ ጥሩ በሆንክበት ሰአት ትወርዳለህ ይሄ ደግም የልጆች ብልጠት ሊሆን ጎል ልታገኝበት የምትችለው አጋጣሚ በእንደዛ በእንደዛ ምክንያቶች የዛሬን ውጤት አጥተናል።

በመጨረሻ ደቂቃ ስለተሻረችባቸው ግብ

“እርግጥ እኔ ርቅያለሁ ፤ ያው የእኛ ግብ ጠባቂዎች ያቁታል ህጉ እና ስርአቱ ይመስለኛል። በዚህ ጉዳይ ላይ ቪዲዮውን ካየው በኃላ ብናገር ደስ ይለኛል ነገርግን አሁን ስላለቀ ለኳሱ ቅርብ የነበሩ የእኛ ልጆች ጎል ነው እያሉኝ ነው ለእኔ ሲታይም በረኛው እጅ ላይ አልገባም ኳሱ ምናልባት ንኪኪ አለው ካለ አላውቅም። ይሄ የዳኛ ውሳኔ ነው ሊሆን የሚችለው እንቀበላለን ፤ በእኛም በዳኞች በኩል ብዙ ስህተቶች አሉብን ይህን እያረምን ለሀገር የተሻለ ተጫዋቾች ለማፍራት እኛም ዳኞቹም እያረምን እንሄዳለን።”


© ሶከር ኢትዮጵያ