ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | አዳማ ከተማ ዲላን አሸንፏል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የአስራ አምስተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ሁለተኛ ጨዋታ አዳማ ከተማ እና ጌዲኦ ዲላ ዲላ ባደረጉት ጨዋታ አዳማ ባለ ድል ሆኗል።

4፡00 ሲል በጀመረው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ በልዩነት ጌዲኦ ዲላ ብልጫን ወስደው የተንቀሳቀሱበት ነበር። ገና 2ኛው ደቂቃ በግራ በኩል ቱሪስት ለማ ሰጥታት እፀገነት ግርማ ያመከነችበት አጋጣሚም ቀዳማሚዋ የጨዋታው ሙከራ ነበረች፡፡ መረጋጋት የተሳናቸው እና ኳስን ይዘው ለመጫወት የተቸገሩ መስለው የታዩት አዳማ ከተማዎች አብዛኛዎቹን ደቂቃዎች ወደ ጌዲኦ ዲላ የሜዳ ክፍል ለማለፍ ሲያደርጉት የነበረው ጥረት ደካማ በመሆኑ የጠሩ የግብ አጋጣሚዎችን መፍጠር አላስቻላቸውም፡፡በአንፃሩ በርካታ ሙከራዎችን ያደረጉት ጌዲኦ ዲላዎች ያገኙት ዕድል በርካታ ቢሆንም በሚያስቆጭ መልኩ በቀላሉ ሲያመክኑት ታይቷል፡፡ በተለይ የአዳማ ከተማ ግብ ጠባቂ ፎዚያ ዝናቡ ጥረቶች ባይታካሉ ኖሮ የተገኙት አጋጣሚዎችን ማስቆጠር በቻሉ ነበር፡፡

18ኛው ደቂቃ ላይ እፀገነት ግርማ ከርቀት እጅግ ጠንካራ ሙከራ አክርራ ስትመታ ግብ ጠባቂዋ ፎዚያ ዝናቡ በአግባቡ መቆጣጠር ባለመቻሏ ከጎሉ ትይዩ የነበረችው ቱሪስት ለማ የተተፋውን ኳስ አግኝታው አስቆጠረች ተብሎ ሲጠበቅ በቀላሉ ወደ ውጪ ሰዳዋለች፡፡ ትዝታ ፈጠነ ከግራ በኩል የመጣላትን ኳስ በሚገባ ከተቆጣጠረች በኃላ በቀላሉ ማስቆጠር የምትችልበትን ዕድል አምክናዋለች፡፡

የምስራች ላቀው ከቅጣት ምት 35ኛው ደቂቃ መታ ግብ ጠባቂዋ መስከረም መንግስቱ ከመለሰችባቸው ሙከራ ውጪ አዳማዎች ይህ ነው የሚባል ተጨማሪ ሙከራን ለማድረግ ተስኗቸው ውለዋል፡፡

ከእረፍት መልስ አሰልጣኝ ሳሙኤል አበራ ያደረገው የተጫዋች ለውጥ አዳማ በመጀመሪያው አጋማሽ ከነበረበት ደካማ አቋም እንዲያገግም ያደረገ ነበር፡፡ ምርቃት ፈለቀ እና ናርዶስ ጌትነትን አስገብተው ቅድስት ቦጋለ እና አስካለ ገብረፃድቅን ካስወጡ በኃላ ልዩነት መፍጠር ችለዋል፡፡ ጌዲኦ ዲላዎች በበኩላቸው እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በወጥነት አቋማቸውን ማሳየት ችለዋል፡፡ ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ አራት ደቂቃ ብቻ እንደተቆጠረ በመልሶ ማጥቃት ቱሪስት ለማ ያለቀለትን ዕድል አግኝታ በቀላሉ አምክናዋለች።

አዳማ ከተማዎች 54ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አግኝተዋል፡፡ ተቀይራ የገባችሁ ምርቃት ፈለቀ ከመሀል ሜዳው ወደ ጌዲኦ ዲላ የሜዳ ክፍል ከተጠጋ ቦታ ያገኘችሁን ኳስ እየገፋች አራት ተጫዋቾችን በማለፍ ብቸኛዋን ግብ ከመረብ አሳርፋለች።

በቀሩት ደቂቃዎች ከእንቅስቃሴ ባሻገር የተለየ ነገርን መመልከት ሳንችል ጨዋታው በአዳማ ከተማ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ