ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አስራ አምስተኛ ሳምንት በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ተካሂደዋል። የተደረጉት ጨዋታዎችን ተመርኩዘንም ክለብ ተኮር ጉዳዮችን እንደሚከተለው ቃኝተናል።

👉 ፋሲል ከነማ አልቀመስ ብሏል

ዐፄዎቹ በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 2ኛ የጨዋታ ሳምንት ላይ በኢትዮጵያ ቡና 3-1 ከተረቱበት ጨዋታ ወዲህ 15ኛ ሳምንት ላይ በደረሰው የሊጉ ውድድር በ12 የጨዋታዎች ምንም ሽንፈትን አላስተናገዱም። በዚህ አስደናቂ ጉዟቸው ውስጥ ሁለት ጨዋታ ብቻ አቻ ሲለያዩ ቀሪዎቹን 10 ጨዋታዎች ድል አድርገዋል።

በአማካይ በጨዋታ 0.6 ግቦችን ብቻ እያስተናገደ የሚገኘው ይህ ቡድን አስደናቂ የውድድር ዘመን በማሳለፍ ላይ ይገኛል። በሁለተኛው ዙር ጅማሮ በመጀመሪያ ሁለት ግጥሚያዎቹ ሁለቱን ቀጥተኛ የዋንጫ ተፎካካሪዎቹን ከአንድ ሳምንት ባጠረ ጊዜ የገጠመው ፋሲል በሁለቱም ጨዋታዎች ድል በማድረግ እጅግ ወሳኝ ስድስት ነጥቦችን ማሳካት ችሏል።

እርግጥ ነው ቡድኑ በሁለቱም ጨዋታዎች በሙሉ ዘጠና ደቂቃ ወጥ እንቅስቃሴን ማሳየት ባይችልም እንደ ትክክለኛ የዋንጫ ቡድን በተቸገረበት የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ በጭማሪ ደቂቃ በተገኘ ግብ ሲያሸንፍ ኢትዮጵያ ቡናን በረታበት ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ ብልጫ ተወስዶበትም ውጤቱን አስጠብቆ መውጣት አልተሳነውም።

የሊጉ ውድድር ገና ቢሆንም ከዚህ በኋላ እየከበደ እንደሚሄድ ይገመታል። ታድያ ፋሲሎችም አሁን የጀመሩትን ጉዞ ለማስቀጠልና በእጃቸው የሚገኘውን ዕድል ላለማባከን ጠንካራ ፈተና ከፊታቸው የሚጠብቃቸው ይሆናል። በቀጣዩ የጨዋታ ሳምንትም በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘውን ጅማ አባ ጅፋርን የሚገጥሙ ይሆናል።

👉 እንደ ቡድን እያጎለበተ የመጣው ወላይታ ድቻ

ከመጨረሻዎቹ ስድስት ጨዋታዎች አምስቱን ማሸነፍ የቻሉት ወላይታ ድቻዎች እንደ ቡድን እጅግ በተለየ የመነቃቃት መንፈስ ላይ ይገኛሉ። የአዲስ አበባ ስታድየሙ የሊጉ ውድድር ሲጠናቀቅ በሊጉ ግርጌ ይዳክር የነበረው ድቻ አሁን ላይ በሊጉ በቀዳሚነት ከሚቀመጡት ወደ አምስቱ ከተቻለውም ወደ ሦስቱ ስለመጠጋት ማሰብ ለመጀመር በቅቷል።

በሌላ ጠንካራ ጎኑም በመጨረሻ አራት ጨዋታዎቹ መረቡን ሳያስደፍር መውጣት ችሏል። በመከላከሉ ረገድ እንደ ቡድን ካለው ጥንካሬ ባልተናነሰ በብዛት ግቦችን አያስቆጥር እንጂ ግቦችን ከሁሉም የሜዳ ክፍል ተሰላፊዎቹ እያገኘ መምጣቱም በጥንካሬ የሚነሳለት ጉዳይ ነው። ነገር ግን በሌላ ጎን ከክፍት ጨዋታ ዕድሎችን ለመፍጠር በጣም እየተቸገረ ይገኛል።

በመጀመሪያዎቹ የጨዋታ ሳምንታት ምርጥ ብቃቱን ያሳየው የቡድኑ ዋነኛ የፈጠራ ምንጭ እንድሪስ ሰዒድ አሁን ላይ ደካማ ጊዜን እያሳለፈ ሲገኝ በመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ለመፍጠር የሚሞክረው ቡድኑ ሲያጠቃ በተጋጣሚ ሳጥን አቅራቢያ በተደጋጋሚ የሚወሰድበት የቁጥር ብልጫ ከክፍት ጨዋታ ግቦች የማግኘት ሒደቱን ከባድ እያደረገበት ይገኛል።

በውድድር አጋማሹ የዝውውር መስኮት ጥሩ ጥሩ የሚባሉ ተጫዋቾችን ያዘዋወረው ድቻ አጥቂው ስንታየሁ መንግሥቱን ከጉዳት መልስ ከማግኘቱ ጋር ተደምሮ በቀጣዮቹ ጊዜያትም ይበልጥ እየጎለበተ ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ከአዳማ ከተማ ብርቱ መከላከል ቢገጥመውም ከቆመ ኳስ መነሻዋን ባደረገች የጋቶች ፓኖም ብቸኛ ግብ ነጥቡን ወደ 20 በማሳደግ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ በቅቷል።

ወላይታ ድቻዎች በ16ኛው ሳምንት የመክፈቻ መርሐ-ግብር ወደ ድል የተመለሱትን እና በአንድ ነጥብ ከድቻ አንሰው ሰባተኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጡት ወልቂጤ ከተማዎች ጋር የሚገናኙበት ጨዋታም ከወዲሁ ተጠባቂ ሆኗል።

👉 ሐይቆቹ እየደረቁ ይሆን ?

በሊጉ አጀማመራቸው ያላማረው ሀዋሳ ከተማዎች ቀስ በቀስ መነቃቃትን አሳይተው ወደ ድንቅ አቋም መጥተው የነበሩ ቢሆንም የዚህኛውን የጨዋታ ሳምንት ጨምሮ ባደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎች በሦስቱ ሲሸነፉ በሦስቱ ደግሞ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።

እንደየተጋጣሚው አጨዋወት ነቢር ነበብ (pragmatic) አቀራረብን የሚከተለው ቡድኑ ጥሩ የውጤት ግስጋሴ ላይ በነበረበት ወቅት የቡድኑ ፈጠራ ምንጭ የነበሩት ሁለቱ የመስመር ተከላካዮች (ተመላላሾች)፣ በአስደናቂ ፍጥነታቸው የግብ ዕድሎችን ከምንም ይፈጥሩ የነበሩት ብሩክ በየነ እና መስፍን ታፈሰ እንዲሁም አስገራሚ አጀማመርን ያደረገው ወጣቱ ወንድማገኝ ኃይሉ እንዲሁም የቡድኑን ሚዛን በአግባቡ ይጠብቅ የነበረው ኤፍሬም ዘካሪያስ ብቻ ብዙዎቹ የቡድኑ የውጤታማነት ሚስጥሮች አሁን ላይ በሚፈለገው ደረጃ ለቡድኑ ውጤት እያበረከቱ አይገኝም።

በደረጃ ሰንጠረዡ ካለው መቀራረብ አንፃር የአንድ ጨዋታ ድል የሚኖረው አስተዋጽኦ የሚታወቅ ቢሆንም ሀዋሳ ወደ ወራጅ ቀጠና ይበልጡኑ እየቀረበ ይገኛል። በ16 ነጥቦች 9ኛ ደረጃ የሚገኘው ቡድኑ በአፋጣኝ ነገሮችን ማስተካከል ካልቻለም ራሱን ማደላደል ካልቻለበት የሰንጠረዡ ወገብ ወደ ስጋት ውስጥ መግባቱ የሚቀር አይመስልም።

ሀዋሳ ከተማዎች 16ኛው ሳምንት ላይ ከሌላው የማሸነፍ ግዴታ ካለበት ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የሚገናኙ ይሆናል።

👉 ባህር ዳር የተመቸው ሰበታ ከተማ

በባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታድየም የነበረውን ቆይታ ከሌሎች ቡድኖች ቀድሞ በዚህኛው ሳምንት ያጠናቀቀው ሰበታ ከተማ በከተማዋ በነበረው ጊዜ ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ሁለት አሸንፎ በሁለቱ ደግሞ አቻ በመለያየት ያለሽንፈት አራቱን ሳምንታት አጠናቋል።

ኳስን መቆጣጠር ምርጫው ላደረገው ሰበታ ከተማ የባህር ዳሩ ምቹ የመጫወቻ ሜዳ በጣሙን ተጠቃሚ ያደረገው ይመስላል። እርግጥ ነው አሁንም ቢሆን ከክፍት ጨዋታ በተለይም አማካይ መስመር ላይ እንደያዛቸው ተጫዋቾች መሀል ለመሀል ዕድሎችን ለመፍጠር እየተቸገረ የሚገኘው ቡድኑ ከመስመር በሚሻገሩ እና በቆሙ ኳሶች አደገኛ እየሆነ መጥቷል።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ሀዋሳ ከተማን የገጠመው ሰበታ በመጀመሪያው አጋማሽ እንደተለመደው በአመዛኙ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ከፍ ያለ የኳስን ቁጥጥር ድርሻ ቢይዝም በቂ የግብ አጋጣሚዎችን መፍጠር አልቻለም። በሁለተኛው አጋማሽ ግን በተለይ በመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት ሰበታዎች ፍፁም ገብረማርያም እና መስዑድ መሀመድ በተቀራራቢ ደቂቃ ባስቆጠሯቸው ግቦች ታግዘው ሀዋሳን መርታት ችለዋል።

በአዲስ አበባ እና በጅማ ቆይታው በወራጅ ቀጣና ፉክክር ውስጥ የሰነበተው የአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ቡድን አሁን ላይ ለሰንጠረዡ አጋማሽ ቀርቦ ወደ ረጅሙ ዕረፍት አምርቷል።

👉 የመከላከል አደረጃጀቱ ተስተካክሎ የታየው እና የፊት መስመሩ በአባካኝነት የቀጠለው ድሬዳዋ

በቅርቡ የአሰልጣኝ ለውጥ ካደረጉ ቡድኖች አንዱ የሆነው ድሬዳዋ ከተማ ከቀደመው አሰልጣኝ ከተረከቡት ቡድን ብዙም ለውጥ ባያደርጉም አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ቡድኑ ላይ አንዳች የራስ መተማመንን እየፈጠሩ ያለ ይመስላል።

በአዲሱ አሰልጣኝ ስር እስካሁን ሦስት ጨዋታዎችን ያደረጉት ድሬዳዋ ከተማዎች ምንም እንኳን በሦስቱም አቻ ቢለያዩም ቡድኑ ላይ የሚታየው መንፈስ ግን እየተሻሻለ ነው። በመከላከል አደረጃጀት ላይ ይስተዋልበት የነበረውን ሰፊ ችግር በአፋጣኝ መፍታት የቻሉት አሰልጣኙ ቡድኑ ከጨዋታ ጨዋታ እንደ ቡድን በሚከላከልበት መንገድ ላይ ለውጦችን እያመጣ ለተጋጣሚዎች በቀላሉ ለመሰበር አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል። በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ የነበረው የፍሬዘር ካሣ እና ያሬድ ዘውድነህ ጥምረትም የተጋጣሚያቸው አጥቂዎች ምንም እንዳይፈጥሩ አግዶ ውሏል።

አሁንም ቢሆን ግን ፈጣን አጥቂዎችን የያዘው ቡድኑ በተጫዋቾች አጠቃቀምም ሆነ የሚገኙ ዕድሎችን ወደ ግብ በመቀየሩ ረገድ ብዙ ይቀረዋል። በክፍት ጨዋታ በአጥቂዎቹ አስደናቂ ፍጥነት በመጠቀም ዕድሎችን የሚፈጥረው ቡድኑ ለማመን የሚከብዱ ኳሶችን መሳቱን ቀጥሏል። ከአጠቃቀም አንፃር ግን ፊት ላይ ሙኸዲን ሙሳ ፣ ኢታሙና ኬይሙኒ እና የጁኒያስ ናንጄቦ ሚና ማስተካከያዎችን የሚፈልግ ይመስላል። በወልዋሎ መነሻውን ከመስመር አድርጎ ወደ ውስጥ በመግባት ከፍ ያለ ተፅዕኖ የነበረው ናንጄቦ አሁን የፊት መስመር አጥቂነት ሚና ተሰጥቶታል። በብዛት በፊት እንዲሁም በመስመር አጥቂነት የምናውቀው ሙኸዲን ሙሳ ደግሞ በአስር ቁጥር ሚና እየተጫወተ ይገኛል። ተፈጥሮአዊ የሳጥን አጥቂ እንደሆነ በድሬዳዋ እና በወልዋሎ ያሳየው ኢታሙና በበኩሉ ከግራ የሚነሳ አማካይ ሆኖ እየተመለከትነው ነው። ታድያ ለተመሳሳይነት የቀረቡ ሦስት አጥቂዎችን የያዙት አሰልጣኙ ተጫዋቾቹን ከአዲስ ኃላፊነት ጋር ከማላመድ ይልቅ የተሻሉ ሆነው በታዩባቸው ቦታዎች ላይ በመጠቀም ቡድኑን በቶሎ የሚረዳ አንዳች ስልት መንደፍ የመጀመሪያ የቤት ሥራቸው ሳይሆን አይቀርም።

ከዚህ የጨዋታ ሳምንት በኋላ ሊጉ በሜዳቸው የሚካሄደው ድሬዳዋ ከተማዎች በ16ኛ ሳምንት የመጨረሻ የባህር ዳር መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ ቡናን የሚገጥሙ ይሆናል።

👉 ሠራተኞቹ ወደ ሥራ ተመልሰዋል

ባለፉት ሦስት የጨዋታ ሳምንታት ተከታታይ ሽንፈትን ያስተናገዱት ወልቂጤ ከተማዎች በዚህኛው ሳምንት በፈተና ውስጥ አልፈውም ቢሆን ከሰሞኑ መነቃቃት ላይ የሚገኘውን ጅማ አባ ጅፋርን 2-1 በመርታት ወደ ድል ተመልሰዋል።

ገና በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በተቆጠረባቸው ግብ ከጅምሩ የጨዋታ ዕቅዳቸው ፈተና የገጠመው ወልቂጤ ከተማዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ያስችሏቸው የነበሩ በርካታ የግብ አጋጣሚዎችን ቢፈጥሩም በተጫዋቾቻቸው ደካማ ውሳኔ አሰጣጥ እና በጅማው ግብ ጠባቂ ጥረት ሲመሩ ለመቆየት ተገደው ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ተስፋ ባለመቁረጥ በሙሉ አቅማቸው ማጥቃታቸውን መቀጠል በመቻላቸው ግን ተቀይሮ በገባው አሜ መሐመድ እና ወደ አግቢነቱ በተመለሰው አህመድ ሁሴን ግቦች ከተተከታይ ሽንፈቶች ያገገሙበትን ድል አስመዝግበዋል።

በተሸነፉባቸው ጨዋታዎች እንኳን ጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የሚያስመልክቱን ሠራተኞቹ ታታሪነታቸውን በሚገልፅ መልኩ ወደ አሸናፊነት መመለሳቸው ለቀጣይ ጨዋታዎችም ስንቅ እንደሚሆናቸው ይጠበቃል። ከድሉ በኋላ በ19 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

👉 የባህር ዳር ከተማ ተከታታይ ድል

በውድድር ዓመቱ በተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ ተስኗቸው የቆዩት ባህር ዳር ከተማዎች ከቀጥተኛ የደረጃ ተፎካካሪያቸው ሀዲያ ሆሳዕና ጋር ያደረጉትን ጨዋታ 1 ለ 0 በማሸነፍ አሳክተዋል። የአራተኛ ደረጃንም ከተጋጣሚያቸው ተረክበዋል።

በውድድር ዓመቱ የተጠበቁትን ያህል መጓዝ ከልቻሉ ቡድኖች አንዱ የነበሩት ባህር ዳር ከተማዎች በተለይ በጅማ ቆይታቸው በተከታታይ የአቻ ውጤቶች ማስተናገዳቸውን ተከትሎ ተፎካካሪነታቸው ላይ ጥያቄ ሲነሳ ቆይቷል። በመቀመጫ ከተማቸው እየተካሄደ በሚገኘው ውድድር ደግሞ የተሻለ ጊዜ እያሳለፉ ይገኛሉ። በዚህም ከሦስት ጨዋታ ሰባት ነጥቦችን ማሳካት ችለዋል።

ቡድኑ ላይ የሚነሳው ዋንኛ ጥያቄ ከጨዋታ ወደ ጨዋታ እንዲሁም በጨዋታ መሐል የሚስተዋለው የወጥነት ችግር ነው። ትናንት ሀዲያ ሆሳዕናን ማሸነፍ መቻላቸው በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ተከታታይ ጨዋታ ያሸነፉበት ሆኖ እንዲመዘገብ ያደረገ ሲሆን ይህን ድክመት የማሻሻል መንገድ መጀመራቸውን ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው። በተጨማሪም ቡድኑ በጨዋታ መሐል የሚስተዋለበትን የተነሳሽነት እና ወጥነት ችግር ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ለመቅረፍ ጥረት አድርገዋል። የማሸነፍያ ጎሎች ከዕረፍት በኋላ ማስቆጠራቸው፣ መሪነታቸውን ለማስጠበቅ ከሌላው ጊዜ በተሻለ ትኩረት መጫወታቸው ስለቡድኑ መሻሻል የሚናገሩ ናቸው።

ባህር ዳር በከተማው የሚያደርገውን ቆይታ በአስራ ስድስተኛ ሳምንት ከአዳማ ከተማ በሚያደርገው ጨዋታ የሚያጠናቅቅ ሲሆን ሦስተኛ ድሉን በማስመዝገብ መሻሻሉን ይቀጥላል ወይ የሚለው የሚጠበቅ ጉዳይ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ