“ገና ብዙ መሥራት ይጠበቅብኛል” – ዮርዳኖስ ምዑዝ

ኢትዮ ኤሌክትሪክን በቅርቡ ተቀላቅላ ጥሩ ጊዜ እያሳለፈች የምትገኘው ዮርዳኖስ ምዑዝ ዛሬ ቡድኗ ጠንካራው ንግድ ባንክን እንዲያሸንፉ ያስቻሉ ጎሎች አስቆጥራለች። አጥቂዋ ከጨዋታው በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ ስለ ወቅታዊ አቋሟ ትናገራለች፡፡

በሰፈር ኳስን ከማንከባለል በዘለለ ወደ ተጫዋችነት የተሸጋገረችው በ2008 በመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ውድድር ለትግራይ ክልል ከተመረጠች በኋላ ነው፡፡በወቅቱ በውድድሩ ላይ ታሳይ የነበረውን አስደናቂ ብቃት የተመለከተው በወቅቱ ደደቢትን ያሰለጥን የነበረው አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ተመልክቷት በቀጥታ ወደ ደደቢት እንድትገባ አደረጋት፡፡ በዛኑ ዓመት ብዙም የመጫወት ዕድል ባታገኝም ከክለቡ ጋር የፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮን መሆን ችላ ነበር፡፡

ከደደቢት በመቀጠል ሲዳማ ቡናን በመቀላቀል የክለብ ህይወቷን ያስቀጠለችው ዮርዳኖስ ከ2011 ጀምሮ እስከ ተሰረዘው የውድድር ዓመት ድረስ በመቐለ 70 እንደርታ በጎሎች የታጀበ ጥሩ ጊዜ አሳልፋለች። በያዝነው ዓመት መስከረም ወር መጀመሪያ በመቐለ የተጠናቀቀውን ኮንትራቷን አድሳ ከክለቡ ጋር ልምምድ ብትጀምርም በአካባቢው በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት እስከ ጥር ወር ድረስ ያለ ክለብ አሳልፋ ከቆየች በኃላ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ተቀላቅላለች።

አራት ወሳኝ ግቦችን ለኤሌክትሪክ በማስቆጠር ጥሩ ጊዜ በክለቧ እያሳለፈች የምትገኘው ዮርዳኖስ ዛሬ ረፋድ ኢትዮጵያ ንግድን ኤሌክትሪክ 2ለ0 ሲያሸንፍ ሁለቱንም ጎል ያስቆጠረች ሲሆን ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ስለወቅታዊ አቋሟ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጋለች፡፡

“እስከ አሁን የኤሌክትሪክ ቆይታዬ በጣም ጥሩ ነው፡፡ አዲስ ቡድን ብገባም ከቡድኑ ጋር ለመዋሃድ ጊዜ አልወሰደብኝም። ጥሩ አሰልጣኝም ጋር ነው የመጣሁት ጥሩ ልምምዶች እየተሰጡኝ ስለነበረ የተሰጠኝንም በአግባቡ እየሰራሁ ስለምገኝ ጥሩ ጊዜ ላሳልፍ ችያለሁ።

“መቐለ ከነበረው ችግር አንፃር ብዙም አልተዘጋጀሁም። እዚህ መጥቼ ነው ልምምድ መስራት የቻልኩት። አሰልጣኝ መሠረትም ከየት እንደመጣሁ ስለምታውቅ ልምምድ ሰዓት ላይ ብዙ ጫና አላሳደረችብኝም። ግን መስራት ያለብኝን ነገር እየነገረችኝ እየደገፈችኝ ጥሩ ጊዜ እንዲኖረኝ አድርጋኛለች፡፡

“ገና ብዙ መስራት ይጠበቅብኛል። በቀጣይ ጊዜ ከዚህ የተሻለ በመሆን ክለቤን ለማገልገል እና ለመጥቀም እፈልጋለሁ። ክለቤን ውጤታማ አድርጌ መጨረስን ነው የምፈልገው። ቻምፒዮን ለማድረግም እፈልጋለሁ”፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ