​ሪፖርት | ወልቂጤ እና ወላይታ ድቻ ነጥብ ተጋርተዋል

የአስራ ስድስተኛ ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመክፈቻ መርሐ-ግብር የሆነው የወልቂጤ ከተማ እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ 1-1 በሆነ ውጤት ተገባዷል።

በ15ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ከመመራት ተነስተው ጅማን ያሸነፉት ወልቂጤ ከተማዎች ሦስት ነጥብ ካገኙበት ጨዋታ ሁለት ለውጦችን አድርገው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በዚህም ዮሃንስ በዛብህን በጀማል ጣሰው እንዲሁም ተስፋዬ ነጋሽን በይበልጣል ሽባባው ተክተዋል። አዳማ ከተማን አንድ ለምንም አሸንፈው ለዚህኛው ጨዋታ የቀረቡት ወላይታ ድቻዎች በበኩላቸው እንድሪስ ሰዒድ ፣ ነፃነት ገብረመድህን እና ቢኒያም ፍቅሩን በስንታየሁ መንግሥቱን ፣ መሳይ አገኘሁ እና በረከት ወልዴ ለውጠው ለጨዋታው ቀርበዋል።

ገና ጨዋታው እንደተጀመረ የወልቂጤን የግብ ክልል በፈጣን የመስመር ላይ እንቅስቃሴ መፈተሸ የጀመሩት ወላይታ ድቻዎች ከመዓዘን ምት ባገኙት አጋጣሚ ገና በጊዜ መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር። በተቃራኒው ኳስን በአንፃራዊነት በተሻለ በመቆጣጠር ጨዋታውን የጀመሩት ወልቂጤዎች በአምስተኛው ደቂቃ ያሬድ ታደሰ ወደ ጎል በመታው የቅጣት ምት የመጀመሪያውን መከራ አድርገዋል። 

ጥንቃቄ የታከለበት እንቅስቃሴ ማድረግ የቀጠሉት ድቻዎች በ11ኛው ደቂቃ መሪ የሆኑበትን ጎል አግኝተዋል። በዚህ ደቂቃም ከጉዳት የተመለሰው ስንታየሁ መንግሥቱ መሳይ አገኘው ያቀበለውን ኳስ የግብ ዘቡ ጀማል ጣሰውን አቋቋም ተመልክቶ ከሳጥኑ ጫፍ ወደ ጎል መትቶ አስቆጥሯል። ጨዋታው ገና ሩብ ሰዓት ሳይሞላው መመራት የጀመሩት ወልቂጤዎች በቶሎ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። በዋናነትም ከአብዱልከሪም የሚነሱ የመሐል ለመሐል ኳሶችን ወደ ግብነት ለመቀየር ሲታትሩ ተስተውሏል። በተቃራኒው ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚደረግ ሽግግር አደገኛ ሆነው የታዩት ድቻዎች በ21ኛው ደቂቃ መሪነታቸውን ወደ ሁለት የሚያሰፉበትን ዕድል አግኝተው ነበር። በዚህም በፈጣን ሩጫ በቀኝ መስመር የገባው ቸርነት ጉግሳ ወደ መሐል ጥሩ ኳስ አሻምቶ ፀጋዬ ብርሃኑ አጋጣሚውን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ከመሐል ለመሐል በተጨማሪ የመስመር ላይ ጥቃቶችን ለግብ ማስቆጠሪያነት መጠቀም የጀመሩት ወልቂጤዎች በ29ኛው ደቂቃ ወደ ጨዋታው የተመለሱበትን ኳስ ከመረብ አገናኝተዋል። በዚህ ደቂቃም የቀኝ መስመር ተከላካዩ ይበልጣል ሽባባው ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ አህመድ ሁሴን በቄንጥ የቡድኑን የአቻነት ጎል አስቆጥሯል። አጥቂው ግቡን ሲያስቆጥር ከጨዋታ ውጪ የሆነ አቋቋም ላይ የነበረ ቢሆንም ግቡ ሊፀድቅ ችሏል። ለአራት ተከታታይ ጨዋታዎች መረባቸውን ሳያስደፍሩ የነበረው ወላይታ ድቻዎች ግብ ካስተናገዱ በኋላ ፈጣኝ ምላሽ በአንድ ደቂቃ ውስጥ ለመስጠት ጥረዋል። በዚህም ከ25ኛው ደቂቃ በኋላ ከፀጋዬ ጋር ቦታ የተቀያየረው ቸርነት በቀኝ መስመር የደረሰውን ኳስ መረብ ላይ ለማሳረፍ ጥሮ መክኖበታል። ቀሪ የመጀመሪያው አጋማሽ ደቂቃዎችም የጠራ የግብ ሙከራ ሳይስተናግድባቸው አንድ ለአንድ በሆነ የአቻ ውጤት ተጠናቋል።

የሁለተኛውን አጋማሽ በተሻለ ተነሳሽነት የጀመሩት ወልቂጤዎች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በመዓዘን ምት እና በተሻጋሪ ኳሶች መሪ ለመሆን ታትረው ነበር። የጨዋታውን የኃይል ሚዛንም ወደ ራሳቸው በማድረግ ሲንቀሳቀሱ ተይቷል። በተቃራኒው ወደ ግብ ክልላቸው አፈግፍገው አጋማሹን የጀመሩት ድቻዎች በ56ኛው ደቂቃ ቸርነት የወልቂጤ ተከላካዮችን የኳስ ቅብብሎሽ አቋርጦ ወደ ጎል በመሄድ ግብ ለማስቆጠር በሞከረው ኳስ የአጋማሹን የመጀመሪያ ጥቃት ፈፅዋል። 

በአንፃራዊነት ቀዝቀዝ ያለ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የነበረው የሁለተኛው አጋማሽ የበዛ የግብ ሙከራ ሳያስተናገድ በአካላዊ ጉሽሚያዎች ታጅቦ ተከናውኗል። ከዚህ መነሻነትም ቸርነት እና ደጉ በድቻ በኩል ረመዳን እና አብዱልከሪም ደግሞ በወልቂጤ በኩል ተጎድተው ከሜዳ ወጥተዋል። ሁለቱም ቡድኖች ጥንቃቄን ተቀዳሚ ምርጫቸው በማድረግ ሲንቀሳቀሱም ታይቷል። በአንፃራዊነት ግን ወልቂጤዎች ከኳስ ጋር የነበራቸውን ጊዜ በማሳደግ ተጫውተዋል። 

የጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ረጃጅም ኳሶችን አዘውትረው የተጠቀሙት ድቻዎች የወጠኑት ዘዴ በወልቂጤ ረጃጅም ተከላካዮች ሲከሽፍ ታይቷል። ጨዋታውም ሌላ ለግብነት የቀረበ ሙከራ ሳያስመለክት 1-1 ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ወልቂጤ ከተማ ነጥቡን 20 በማድረስ ያለበት 7ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ወላይታ ድቻ ደግሞ በሰበሰባቸው 21 ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ ፀንቶ ተቀምጧል።