​የአሰልጣኞች አስተያየት | ወልቂጤ ከተማ 1-1 ወላይታ ድቻ

የ16ኛው ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኞች ለሱፐር ስፖርት የሰጡት አስተያየት ይህንን ይመስላል።

አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው – ወልቂጤ ከተማ

ስለጨዋታው

በዛሬው ጨዋታ ሦስት ነጥብ ይዘን ለመሄድ ነበር በቁርጠኝነት ወደ ሜዳ የገባነው። ይዘን የገባነውን ጨዋታ በአግባቡ ለመታግበር ጥረት እያረግን ባለንበት ሰዓት ነው ቅድሚያ ጎል ያስተናገድነው። ያ ጎል ልጆቹ ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ አሳድሯል። ሆኖም ግን እንደ ጨዋታው ክብደት በፈለግነው ልክ በተደጋጋሚ ጎል ላይ መድረስ አልቻልንም። ሦስተኛውን የሜዳ ክፍል ሰብረን ለመግባት የተቸገርንበት እንቅስቃሴ ነው የነበረው። ሆኖም ግን ውጤቱን ቀልብሰን በአቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል።

ስለ አብዱልከሪም ወርቁ እና ረመዳን የሱፍ ጉዳት

ያው ዳኛው ጨዋታው ላይ ንክኪ ፈቅደዋል። ኃይል የተቀላቀለበት ጨዋታ ነው የነበረው። እነሱ የመረጡት ጨዋታ በዚህ መንገድ ቡድኑን እናቆመዋለን የሚል ሊሆን ይችላል ፤  አላውቅም። ሆኖም ግን የእኛ ልጆች ከኳሱ ጋር ምቾት ተሰምቷቸው ለመጫወት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ትልቅ ሳንካ ነው ገጥሞን የነበረው። በአጠቃላይ ግን የነበረው የአየር ሁኔታ ፀሀዩም በጣም ጠንካራ ነው። ሜዳው ደረጃውን የጠበቀ ሜዳ ነው ፤ ኢኮኖሚካል በሆነ ሁኔታ ተጫውተን ለመሄድ ነበር በአብዛኛው ፈጣሪ ተጫዋቾችን ለማስገባት ጥረት ያደረግነው። በፈለግነው ልክ ተጫውተናል ብዬ አላስብም ያገኘነው ውጤት አያስከፋም።

አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው – ወላይታ ድቻ

በውጤቱ ደስተኛ ስለመሆናቸው

በጨዋታው ደስተኛ ነኝ። ምክንያቱም በፈለግነው ልክ በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ውጪ መረቡን አልፈን ፍፁም ያለቀላቸው የግብ ዕድሎች አግኝተናል። ያለመጠቀም ድክመታችን እንዳለ ሆኖ ማለት ነው። የመከላከል አደረጃጀታችን ግን ከወትሮው ቀዝቅዝ ያለ ነው። ጎልም ሲገባብን አንዱ ምክንያት ያ ነበር። ከዕረፍት በኋላ በእርግጥ ታክቲካሊ ለውጥ አድርገናል። እነሱ በፈለጉት መንገድ ሰብሮ የመግባቱ ነገር አልነበረም። ዞሮ ዞሮ መልካም ነው። ከሌላው ጊዜ ፍፁም ለጎል የቀረቡ በጨዋታ ሂደት የሚፈጠሩ ኳሶችን አግኝተናል። ይህ ቡድኑ ላይ ከዚህ በፊት ያልነበረ ነው። ዛሬ ጥሩ ነው ብሎ መናገር ይቻላል።

ስለስንታየሁ መንግሥቱ ግብ ማስቆጠር

በዚህ በጣም ደስተኛ ነኝ። ምክንያቱም ልጁ ከፍተኛ የሆነ ጉጉት አለው። ዛሬም መቶ ፐርሰንት ለጨዋታው አልደረሰም። ግን ከፍተኛ ጉጉት ስለነበረው አንዳንዴ ተጫዋች ፍላጎቱ ከፍተኛ ሲሆን የእኛም እገዛ ያስፈልገዋል እና እንዲጠቀም እንዲገባ አድርገናል አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ ጎልም አስቆጥሯል። በእሱ ጎል ነው ነጥብ የተጋራነው። ዛሬ መግባቱ ብሎም ማግባቱ የሚፈጥርበት ነገር አለ።

ስለባህር ዳር ቆይታቸው

የባህር ዳር የመጨረሻ ቆይታችንን ጎላችንን በማስደፈር ዘግተናል። የባህር ዳር ቆይታችን በጣም ደስ የሚል ነው። ህዝቡም ከተማይቱም ኢትዮጵያዊነት ያየንበት ነበር። ጎሉ ባይቆጠር ደግሞ ደስታችን የበለጠ እጥፍ ድርብ ይሆን ነበር። በጥቅሉ ግን ደስተኛ ነኝ። 

© ሶከር ኢትዮጵያ