“በመጀመሪያው ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ፈትኖን ነበር” – አኒሴት አንድሪያናንቴኒያና

የዋልያዎቹ ቀጣይ ተጋጣሚ ማዳጋስካር አምበል የሆነው አኒሴት አንድሪያናንቴኒያና ከቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ ጋር ባደረገው ቆይታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጠንካራ እንደሆነ ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ካሜሩን ለምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎቹን እያከናወነ እንደሆነ ይታወቃል። ቡድኑም መጋቢት 15 እና 21 ከማዳጋስካር እና ኮትዲቯር ጋር የምድቡ ወሳኝ አምስተኛ እና ስድስተኛ ጨዋታዎቹን ባህር ዳር እና አቢጃን ላይ ያከናውናል። አሠልጣኝ ውበቱ አባተም ለጨዋታዎቹ ይጠቅሙኛል ያሏቸውን 25 ተጫዋቾች ከትላንት በስትያ መጥራታቸው ይታወሳል።

የቡድኑ የመጀመሪያ ተጋጣሚ ማዳጋስካርም ባሳለፍነው ሳምንት የመጨረሻ ቀን ለ30 ያህል ተጫዋቾች (4 የግብ ዘብ፣ 9 ተከላካይ እና አማካይ እንዲሁም 8 አጥቂ) ጥሪ ማቅረቧ ተሰምቷል። ጥሪ ውስጥ ከተካተቱት ተጫዋቾች መካከል የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ አኒሴት አንድሪያናንቴኒያና ይገኝበታል። በአሁኑ ሰዓት ለቡልጋሪያው ሉዶጎሬትስ ራዝጋርድ እየተጫወተ የሚገኘው የ30 ዓመቱ የብሔራዊ ቡድኑ አምበል አኒሴት ስለ ኢትዮጵያው ጨዋታ ከቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ ጋር ቆይታ አድርጓል።

“በመጀመሪያው ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ፈትኖን ነበር። እርግጥ ጨዋታውን አንድ ለምንም ብናሸንፍም አብዛኛውን የጨዋታ ደቂቃ እነሱ በልጠውን ነበር። ግን የእግርኳስ ነገር ሆነ እና አሸነፍን። ቀጣዩም ጨዋታ ቀላል እንደማይሆን አስባለሁ።

“የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾች አሉት። ከሁለት ወይንም ሦስት ተጫዋቾች ወጪም አብዛኞቹ በሀገር ውስጥ የሚጫወቱ ናቸው። ጨዋታውም ጥሩ ፉክክር የሚታይበት ይመስለኛል። ግን እነሱ ሊፈትኑን እንደሚችሉ እናውቃለን። ስለዚህ እኛ በጨዋታው ዝግጁ ሆነን ምላሾችን መስጠት አለብን።

“ማዳጋስካር ላይ ቡድኑ ምን አይነት እንደሆነ እና በምን መልኩ መጫወት እንደሚችል አይተናል። ስለዚህ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንክረን መቅረብ አለብን። ከምንም በላይ ግን የአዕምሮ ዝግጁነት ወሳኝ ነው። ሁላችንም አንድ ከሆንን ጨዋታውን እንወጣዋለን።”ብሏል።

2019 በተደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈችው ማዳጋስካር በ2015ቱ የውድድሩ አሸናፊ ኮትዲቯር በእርስ በእርስ ግንኙነት ተበልጣ የምድቡ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ትገኛለች። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በአንድ ነጥብ አንሶ (6) ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በምድቡ አንድ ጨዋታ ብቻ ድል ያደረገችው ኒጀር በበኩሏ ሦስት ነጥቦችን ብቻ በመያዝ የመጨረሻውን ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።