ቤትኪንግ የኢትዮጰያ ፕሪምየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ቁጥሮች እና ዕውነታዎች

በአስራ ስስስተኛው ሳምንት ቤትኪንግ የኢትዮጰያ ፕሪምየር ዙርያ ቁጥራዊ መረጃዎች እና ዕውነታዎችን እንደሚከተለው አሰናድተናል።

የጎል መረጃዎች

– በዚህ ሳምንት በተደረጉት ስድስት ጨዋታዎች 13 ጎሎች ተቆጥረዋል። ካለፈው ሳምንት በአራት ከፍ ያለ የጎል ቁጥርም ተመዝግቧል።

– ባለፉት ሳምንታት ከዕረፍት በኋላ የሚቆጠሩ ጎሎች በርከት ብለው ሲታዩ የነበረ ቢሆንም በዚህ ሳምንት የመጀመርያ አጋማሽ ጎሎች አመዝነው ታይተዋል። ከአስራ ሦስቱ ጎሎች መካከል ዘጠኝ ጎሎች የተቆጠሩትም ከዕረፍት በፊት ነው።

– እንዳለፈው ሳምንት ሁሉ በዚህ ሳምንትም የፍፁም ቅጣት ምት ጎል አልተመዘገበም።

– ከአስራ ሦስት ጎሎች መካከል ከአንዱ በቀር በክፍት የጨዋታ እንቅስቃሴ ሲቆጠሩ ቢስማርክ አፒያ ከቅጣት ምት መነሻነት ያስቆጠረው ብቸኛ ጎል ብቸኛው ከቆመ ኳስ መነሻነት የተቆጠረ ነው።

– እንዳለፈው ሳምንት ሁሉ በዚህም ሳምንት ሁለት ጎሎች በጭንቅላት ተገጭተው ተቆጥረዋል። የሊጉን ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትን በአንደኝነት እና ሁለተኝነት የሚመሩት አቡበከር ናስር እና ሙጂብ ቃሲም ናቸው የጎሎቹ ባለቤቶች።

– የባህር ዳር ከተማው ፍፁም ዓለሙ እና የወላይታ ድቻው ስንታየሁ መንግሥቱ ከሳጥን ውጪ መትተው ጎል ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።

– 12 ተጫዋቾች በጎል አስቆጣሪነት ስማቸውን አስመዝግበዋል። ሙጂብ ቃሲም በሁለት ጎል ከፍተኛው አስቆጣሪ ነው።

– መድኃኔ ብርሃኔ እና እንዳለ ደባልቄ በውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ጎላቸውን አስቆጥረዋል።

– አስር ተጫዋቾች ለጎል በማመቻቸት አስተዋፅኦ ሲያደርጉ አቡበከር ናስር ጎል እና አሲስት በማስመዝገብ ብቸኛው ነው።

የዲሲፕሊን ቁጥሮች

– የሚመዘዙ የማስጠንቀቂያ ካርዶች ብዛት ከሳምንት ሳምንት እየቀነሰየ ይገኛል። በዚህ ሳምንት 12 ካርዶች ሲመዘዙ ይህም በአስራ አንድ የቀነሰ ነው።

ዕውነታ

– ዑመድ ኡኩሪ ከስድስት ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ አድርጓል። አጥቂው ለመጨረሻ ጊዜ በፕሪምየር ሊጉ ጨዋታ ያደረገው ሰኔ 16 ቀን 2006 ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 1-0 ባሸነፈበት ጨዋታ ሲሆን ከስድስት ዓመት፤ ከስምንት ወራት ቆይታ በኋላ ሀዲያ ሆሳዕና ሲዳማን 2-0 በረታበት ጨዋታ ላይ መሰለፍ ችሏል።

የሳምንቱ ስታቶች

(ቁጥሮቹ የተገኙት ከሱፐር ስፖርት ነው)

ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ

ከፍተኛ – ኢትዮጵያ ቡና እና ፋሲል ከነማ (7))
ዝቅተኛ – አዳማ ከተማ (0)

ጥፋቶች

ከፍተኛ – አዳማ ከተማ (19)
ዝቅተኛ – ኢትዮጵያ ቡና (7)

ከጨዋታ ውጪ

ከፍተኛ – ድሬዳዋ ከተማ (7)
ዝቅተኛ – ቡና እና ጅማ (0)

የማዕዘን ምት

ከፍተኛ – ሀዋሳ እና ጊዮርጊስ (8)
ዝቅተኛ – ድሬዳዋ እና ጅማ (1)

የኳስ ቁጥጥር ድርሻ

ከፍተኛ – ኢትዮጵያ ቡና (74%)
ዝቅተኛ – ድሬዳዋ ከተማ (26%)


© ሶከር ኢትዮጵያ