“ኢትዮጵያን በሜዳዋ መግጠም ከባድ እንደሆነ በደንብ አረጋግጠናል” – ኒኮላ ዱፑይ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን አራት ለምንም አሸናፊ ካደረገው ጨዋታ መገባደድ በኋላ የማዳጋስካር ዋና አሠልጣኝ ኒኮላ ዱፑይ የድህረ-ጨዋታ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

“በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ። ቡድኑም ጥሩ ቡድን ነው። በጨዋታውም ማሸነፍ ይገባችኋል። በጨዋታው ምንም ምክንያት ማስቀመጥ አልፈልግም። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የእኛን ቡድን በልጧል። ኢትዮጵያን በሜዳዋ መግጠም ከባድ እንደሆነም በደንብ አረጋግጠናል። ምንም ቢሆን ግን የቡድኔን ተጫዋቾች ማመስገን እፈልጋለሁ። በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎችም አንድ እና ሁለት ጎሎችን ማስቆጠር እንችል ነበር። ግን አልተጠቀምንበትም። በዚህም በኋላ ላይ ተቀጥተናል። በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥሩ ተጫውቷል።

“ከጨዋታው በፊት ከባድ ፍልሚያ እንደሚጠብቀን አስበን ነበር። ምክንያቱም አንታናናሪቮ ላይ ቡድኑ ሲጫወትበት የነበረውን መንገድ አይተናል። በተጨማሪም ቡድኑ ኮትዲቯር እና ኒጀርን ኢትዮጵያ ላይ እንዳሸነፈ እናውቃለን። ከእነዚህ መነሻነት ከባድ ጨዋታ እንደሚጠብቀን ቀድመን ተገንዝበናል። ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለዝግጅት ረዘም ያለ ጊዜ አግኝቷል። እኛ ግን የሁለት ቀን ዝግጅት ብቻ ነበር ያደረግነው። በተጨማሪም በኮቪድ-19 እና የፊፋ ክልከላ ቋሚ ተጫዋቾቻችንን ሙሉ አላገኘንም። በቀጣይ ከኒጀር ጋር ለመጫወት ሥድስት የዝግጅት ቀናት ይኖሩናል። በቀጣዩም ጨዋታ የተሻለ ነገር ለማምጣት እንሞክራለን። በመጨረሻ ግን በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ ለተጫወቱት ተጫዋቾቼ በድጋሜ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ።”


© ሶከር ኢትዮጵያ