የዋልያዎቹ የደስታ መልዕክቶች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደመሠረተው የአፍሪካ ዋንጫ ሲመለስ የዋልያዎቹ አሠልጣኝ እና ተጫዋቾች ያጋሩትን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ሰብስበን ይዘን ቀርበናል።

በምድብ 11 ተደልድሎ ካሜሩን ለምታስተናግደው የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎችን ሲያከናውን የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በትናንትናው ዕለት ሦስት ለአንድ ያሸነፈውን የአይቮሪኮስት ብሔራዊ ቡድንን ተከትሎ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ማለፉን አረጋግጧል። ጮቤ ከሚያስረግጠው አጋጣሚ በኋላም የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ እና ተጫዋቾች በግል ማኅበራዊ ገፆቻቸው ያስተላለፏቸውን የደስታ መልዕክት ሰብስበን ይዘን ቀርበናል።

የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ

“ውድ ኢትዮጵያውያን ሀገራችን የብስራት ዜና መስማት ብርቅ በሆነባት በዚህ የጭንቅ ወቅት በእግር ኳሱ ዘርፍ ለ8 አመት ከራቅንበት መድረክ ላይ በድጋሚ መገኘት የመቻላችን ዜና በመላው ህዝባችን ዘንድ የፈጠረውን ደስታ በማየቴ ቸሩ ፈጣሪዬን አመሰግነዋለሁ። እኛ የስፖርት ሰዎች ነን የተሰበሰብነው ከተለያየ የሀገሪቷ ክልሎች ከተለያየ ሀይማኖቶች እና ከተለያየ ክለቦች ቢሆንም በመሃላችን አንድም መከፋፈል ሳይኖር በኢትዮጵያ ባንዲራ ስር አንድ በመሆን ለጋራ ድል በሞያችን አገራችንን ለማገልገል ተሰልፈን በፈጣሪ እርዳታ አገራችንን አንድ ደረጃ ለማድረስ ተግተናል። ፈጣሪ ሳያሳፍር እዚህ አድርሶናል በኢትዮጵያዊነት ዘምረናል በየብሄር ዘፈኖች ጨፍረናል ተቃቅፈን ፈጣሪን ለምነናል አድርጎልን ሀሴት አድርገናል። እኛ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ነን ግዳጃችንን በሚገባ ተወጥተን ለሀገራችን ከፍታ በሞያችን በአንድነት የቆምን። እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ ህዝብ ከዚህም በላይ ደስታ ይገባዋል። በሞያችን ሁሌም ሀገራችንን ከፍ ለማድረግ ከሌሎች ያደጉ አገሮች ተርታ ለማሰለፍ የሚቻለንን ሁሉ እናደርጋለን ። ሁሉም ለሀገሩ በተሰማራበት የሞያ ዘርፍ የበኩሉን ከተወጣ የሻለች ኢትዮጵያን መፍጠር እንችላለን በመጨረሻም ለዚህ ድል እንድንበቃ ከጅምሩ በማጣሪያው ለተሳተፉ መላው ተጨዋቾች ለኢንስትራክተር አብረሀም መብራቱ እና አብረውት ለነበሩ የአሰልጣኝ አባላት በሙሉ ይህ ድል የናንተ የስራ ጅምር ጭምር በመሆኑ ምስጋና ይገባችኃል። ይህንን ከባድ የሀገር አደራና ሀላፊነት በአስቸጋሪ ወቅት እንድረከብ በእኔ ላይ በማመን ሀላፊነቱን ለወሰዳችህና በስራዬ ስትደግፉኝ ለነበራችሁ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስር አመራርና የፅ/ቤት ሰራተኞች በሙሉ ላሳያችሁት ከፍተኛ ድጋፍ ትብብር በራሴ እንድተማመንና ለዚህ ድል እንድንበቃ በማስቻላችሁ ከልብ ማመስገን እፈልጋለሁ። ምንም እንኳን በዚህ ጊዜ በተለያየ ምክንያት አብረን ባንሆንም ከምርጫ እስከ ዛሬዋ የመጨረሻ ቀን ድረስ በፀሎትና በመልካም ምኞት አብራችሁን ለነበራችህ ተጨዋቾች በሙሉ ይህ ድል የናተም ጭምር በመሆኑ ልትደሰቱ ይገባል። በሊጉ የምትገኙ አሰልጣኞች የክለብ ሃላፊዎች በሙሉ ይህ ድል የናንተም የስራ ውጤት በመሆኑ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ ። መላው የስፖር ወዳድ ቤተሰብ በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጪም ያላችሁ ኢትዮጵያዊያን ፀሎታችሁ ስለተሰማ አብራችሁን ስለነበራችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ። በስራው ላይ አብራችሁኝ ሌት ተቀን የደከማችሁ የስልጠና ቡድን አባላት እና በተለያየ ዘርፍ ስታግዙን የቆያችሁ ባለሞያዎች ለነበራችሁ ቀናነትና ያላችሁን ሙያ ለቡድኑ በማበርከት ቡድናችን ለዚህ እንዲበቃ በማድረጋችሁ በኢትዮጵያ ህዝብ ስም ከልቤ አመሰግናችኋለሁ። ውድ ባለቤቴና የልጆቼ እናት ወ/ሮ ውባለም ወ/ወርቅ እና ልጆቼ እህትና ወንድሞቼ ቤተሰቦቼ አብሮ አደግ ጓደኞቼ እኔ እንድሻሻል እንዳድግ በሁሉም ዘርፍ ስትደግፉኝ ስትረዱኝ ስትፀልዩልኝ ለነበራችሁ ሁሉ ፈጣሪ ብድራችሁን ይክፈላችሁ። በመጨረሻም ቸሩ መዳህኒያለም ክብር ሁሉ ላንተይሁን ። ፈጣሪ ሀገራችንን ሰላም ያድርግልን ከፍታዋን ደግሞ ደጋግሞ ያሳየን የኢትዮጵያ ትንሳኤ እሩቅ አይደለም።”

አስቻለው ታመነ

“ለዚህ ምስኪን ህዝብ ይሄ ደስተቀ ቢያንስበት እንጂ አይበዛበትም !

ኢትዮጵያዊነት መገለጫ ቀለሙ ብዙ ነው!
ሁላችንም በሙማሜማችን ጠንክረን ሰርተን ሀገራችንን ደስ እናሰኛት።

ድንግል ማርያም እናቴ ለምኜሽ ያሳጣሽኝ ነገር የለም። በዕለተ ቀንሽ ይሄን ጣፋጭ ደስታ ሰጥተሽኛል። አዛኝቷ እናቴ ክብር ላንቺ ይሁን።”

ሙጂብ ቃሲም

“መላው ኢትዮጵያዊ እንኳን ደስ ያለን

ህዝባችንን የዛሬውን ጨዋታ አሸንፈን ደስታውን ድርብ ባለማድረጋችን ብንከፋም በቀጣይ ለዚህ እንቁ ህዝባችን እና እግር ኳስ አፍቃሪ ደስታውን እጥፍ ድርብ ለማድረግ ጠንክረን ከወዲሁ እንሰራለን።”

ሽመልስ በቀለ

” ‘እውነትም ማታ ነው ድላችን’ ”

መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎናችን ስለነበራችሁ ከልብ አመሠግናለሁ። ይህ ውጤት ውድ ጊዜያችሁን ሰውታችሁ እንደ ቀደሙት ዓመታት እና እንደ ሁል ጊዜውም ሁሉ ከጎናችን ለነበራችሁ ሁሉ ይገባችኋል።

ይህ ድል እንዲመጣ ትልቅ ድርሻ የተወጡትን የአሁኑን የአሠልጣኞች ክፍል ጨምሮ የኢ/ር አብርሃም መብራቱን ስብስብ ላቅ ያለ ምስጋናዬን ለማቅረብ እወዳለሁ።

የብሔራዉ ቡድን ተጫዋቾ አለቃው ህዝብ ነው፣ አለቆቻችንን በማስደሰታችን ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶናል።”

ብሔራዊ ቡድኑ የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጉዞውን ሲጀምር የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ የነበሩትና በሰኔ ወር መጨረሻ ከኃላፊነታቸው የተነሱት የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱም በፌስቡክ ገፃቸው የሚከተለውን ብለዋል:-

“እንኳን ደስ ያለን
እንኳን ደስ ያላቹ

ለአሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና ረዳቶቹ፣ ለመላው የቡድኑ አባላትና ተጫዋቾች እንዲሁም አመራሮች በሙሉ፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ ወደ አፍሪካ ዋንጫ መድረክ እንድትመለስ የነበረንን ልባዊ ምኞትና ሀሳብ በተባበረው ህብረታቹ እና ጥንካሬያቹ እንዲሳካ በማድረጋቹ ትልቅ ክብርና ምስጋና ይገባችኋል፤ ድሉ ለሀገራችን አንድነትና ለእግርኳሱ መነቃቃት የሚሰጠው ጥቅም ትልቅ እንደሆነ አምናቹ በቀጣይም ከፊታችን ለሚኖሩን አህጉርአቀፍና አለምአቀፍ ውድድሮች ጠንክራቹ በመስራት የተጀመረውን ድልና ስኬት እንደምታስቀጥሉ ከፍተኛ እምነትና ተስፋ አለኝ።
በድጋሚ እንኳን ደስስስስ ያለን!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿንና ይባርክ”


© ሶከር ኢትዮጵያ