የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የዛሬ ውሎ ዝርዝር

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የሁለተኛው ዙር መርሀግብሮች ቀጥለው እየተደረጉ ሲገኙ የዛሬውን የየምድቦቹን ጨዋታዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፡፡

የምድብ ሀ የአስራ ሦስተኛ ሳምንት መርሀ ግብር ሁለተኛ ቀን ውሎ 3፡00 ሲል የጀመረ ሲሆን ወሎ ኮምቦልቻን ከደሴ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ እልህ አስጨራሽ ፉክክር አስመልክቶን በደሴ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ በሙከራ ረገድ ደሴ ከተማዎች ብልጫን መውሰድ ችለዋል፡፡ በተለይ ረጃጅም ኳሶች ወደ አጥቂዎቹ በመጣል ጎል ለማግኘት ጥረት ያደረጉት ገና ከጅምሩ ነበር፡፡ አብዱላዚዝ ዳውድ ከቅጣት ምት ባደረገው ሙከራ የወሎ ኮምቦልቻን የግብ ክልልም ፈትሸዋል። በፈጣን የሽግግር ኳስ ሌላ ሙከራን 18ኛው ደቂቃ ላይ ዳግም አድርገዋል፡፡ ልዑልሰገድ አስፋው ከተሰለፈበት የግራ መስመር የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ወደ ግብ ሲያሻማ ሳሙኤል ወንድሙ በግንባር ገጭቶ ወደ ውጪ ለጥቂት የግቡን ቋሚ ታካ ወጥታበታለች፡፡

የደሴ ከተማን የቅብብል መንገድ በተወሰነ መልኩ ሲያቋርጡ የነበሩት ወሎ ኮምቦልቻዎች ተመጣጣኝ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ለማሳየት ባይቸገሩም ወደ ተጋጣሚ ሦስተኛ የሜዳ ክፍል ሲደርሱ መረጋጋት ሲሳናቸው ይስተዋል ስለነበር ያገኟቸውን አጋጣሚዎችን እንዳይጠቀሙ አድርጓቸዋል፡፡ በዚህኛው አጋማሽ ቴዲ አጋ ከርቀት ያደረጋት ያልተሳካች ኳስ ቡድኑ በ38ኛው ደቂቃ ያደረገው ብቸኛ ሙከራ ሆና ተመዝግባለች፡፡

ከእረፍት መልስ የደሴ ከተማ የጨዋታ እና የሙከራ የበላይነት ጎልቶ የታየበት አጋማሽ ነበር፡፡በተለይ በአንድ ሁለት ቅብብልም ይሁን ኳሱን ወደ መስመር በማውጣት ወደ ግብ ክልል በመጣል ጎል ለማግኘት የአሰልጣኝ ያሬድ ቶሌራው ቡድን ጥረቶችን በተደጋጋሚ አድርጓል፡፡ በዚህም 78ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አግኝተዋል፡፡ ከቀኝ የሜዳ ክፍል በረጅሙ የተሻገረለትን ኳስ የቀድሞው የድሬዳዋ እና ባህር ዳር ከተማ አጥቂ ፍቃዱ ወርቁ የወሎ ኮምቦልቻ ተከላካዮች አቋቋም ስህተት አግዞት በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር የደርቢው ጨዋታ በደሴ ከተማ 1ለ0 እንዲጠናቀቅ አስችሏል፡፡

መከላከያ ከአንድ ቀን ቆይታ በኃላ በድጋሚ በጎል ተንበሽቦ በጎል ልዩነት መሪነቱን መልሶ መያዙን ያረጋገጠበትን ድል በወልዲያ ላይ አስመዝግቧል። የመከላከያ የጨዋታ ብልጫ እንዲሁም የወልድያ የመከላከል ድክመት የዚህ ጨዋታ የሙሉ ደቂቃው ገፅታ ነበር፡፡ የፌድራል ዳኛ ሚካኤል ጣዕመ ፊሽካ ከተነፋበት ደቂቃ ጀምሮ ረጃጅም ኳስን ከተለያዩ የሜዳው ክፍል ወደ መስመር በማሳለፍ በቁመት ረዘም ላሉት የፊት አጥቂዎች በማሳለፍ በግንባር በሚገጩ ኳሶች ጎሎችን ለማስቆጠር ገና በጊዜ ጥረት ማድረግን የጀመሩበት እንደነበር መመልከት ተችሏል፡፡ጨዋታው ተጀምሮ ሶስት ያህል ደቂቃ እንደተቆጠረ ወልድያዎች ክስ አስመዝግበዋል፡፡ ጋናዊው የመከላከያ አጥቂ ኤርነስት ባራፎ “የዝውውር መስኮቱ ከተጠናቀቀ በኃላ ፈርሞ ነው ወደ ሜዳ የገባው።” በሚል ቡድኑ አቤቱታውን ካቀረበ በኃላ ጨዋታው ቀጥሏል፡፡ ጨዋታውን ከጅምሩ ማፍጠን ላይ ትኩረት ያደረጉት የአሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ ልጆች 6ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አግብተዋል፡፡ ሳሙኤል ሳሊሶ በግራ የወልድያ የግብ ክልል አካባቢ ወደ ጎል ሲያሻማ ኤኒስት ባራፎ በግንባር ገጭቶ ግብ ጠባቂው ምናለ በቀለ ሲመልስበት ዘካሪያስ ፍቅሬ በቀላሉ ከመረብ በማዋሀድ ጦሩን ቀዳሚ አድርጓል፡፡

በመስመር አጨዋወታቸው የዘለቁት መከላከያዎች በተደጋጋሚ እጅጉን የሚያስቆጩ ዕድሎችን ሲፈጥሩ የታዩ ሲሆን የወልድያው ግብ ጠባቂ ምናለ አስደናቂ ብቃት ግን የተደረጉ በርካታ ሙከራዎች ወደ ጎልነት እንዳይለወጡ አድርጓል። ሆኖም የተከላካዮች ዝንጉነት ከመስመር የሚመጡ ኳሶችን መቆጣጠር ባለመቻላቸው ሁለተኛ ጎል ለማስተናገድ ተገደዋል፡፡ የወልድያው ተከላካይ ሀቁምንይሁን ገዛኸኝ ኳስን ለግብ ጠባቂው አቀብላለሁ ብሎ በዞረበት ቅፅበት ከጀርባው የነበረው ዘካሪያስ ፍቅሬ በፍጥነት ነጥቆት እየነዳ ገብቶ ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ጎልን ከመረብ አሳርፏል፡፡

መከላከያዎች በወጥነት የተጠቀሙበት የተሻጋሪ ኳሶች ውጤታማ አድርጓቸው ዘልቋል፡፡ ኤኒስት ባራፎ እና ዘካሪያስ ፍቅሬ በዚህ የጨዋታ ሂደት በመጡ ኳሶች በተደጋጋሚ በተጋጣሚያቸው ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ ታይቷል፡፡ ኤሌክትሪክን ለቆ በሁለተኛው አጋማሽ ወልድያን የተቀላቀለው መስፍን ኪዳኔ በቀኝ በኩል ከመስመር ጠርዝ ከርቀት ያደረጋት ሙከራ እና የመከላከያን የቅብብል መንገድ በማቋረጥ በተገኘ ኳስ የቀድሞው የአርባምንጭ አጥቂ ያሬድ ዳርዛ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መቶ ወደ ውጪ ከወጣበት ውጪ ወልድያዎች በሙከራ ተዳክመው ታይቷል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ይበልጥ ያየሉት መከላከያዎች ከእረፍት መልስ ወልድያዎች በአድናን ረሻድ አማካኝነት 47ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ጨዋታ ለመመለስ የሚረዳቸውን ሙከራ አድርገው አንድ ደቂቃ እንደተቆጠረ ኤኒስት ባራፎ ሲያሻማ ሰለሞን ሀብቴ አግኝቶ ለመምታት ሞክሮ በተከላካዮች ቢነጠቀም አምበሉ በኃይሉ ግርማ እግር ስር ኳሷ በመግባቷ በቀጥታ ከመረብ አገናኝቶ የመከላከያን የጎል መጠን ወደ ሶስት አሳድጓል፡፡

ጎል ለማግኘት ሲያነፈንፉ የዋሉት መከላከያዎች በተደጋጋሚ በኤኒስት ባራፎ እና ዘካሪያስ ፍቅሬ አማካኝነት ሙከራን በማድረጉ ረገድ የተዋጣላቸው ቢሆንም ያገኟቸውን ዕድሎች ግን ለማስቆጠር እጅጉን የአጨራረስ ክፍተት ይስተዋልባቸው ነበር፡፡

እጅጉን ተዳክመው የታዩት ወልድያዎች ለማንሰራራት ያደረጉ የነበረው እንቅስቃሴ ቀዝቃዛ በመሆኑ በተደጋጋሚ አሰልጣኝ መኮንን ገብረዮሐንስ በተጫዋቾቹ ላይ ቅሬታን ሲያሰማ ተመልክተናል፡፡ 78ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው መሐመድ አብዱላሂ ለመከላከያ ምናልባትም ጎል ያስቆጠረ የመጀመሪያው የውጪ ዜጋ ተጫዋች ሆኖ ጨዋታው 4ለ0 ተደምድሟል፡፡ በኢትዮ ኤሌክትሪክ በነጥብ ለአንድ ቀን ተበልጦ የነበረው መከላከያ በነጥብ ዕኩል ሆኖ በጎል በልጦ ወደ መሪነቱ መሸጋገርም ችሏል፡፡

ወልድያ ሼህ አሊ አላሙዲን ስታዲየም እየተደረገ የሚገኘው የምድብ ለ የአስራ አራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ቀጥለው ተካሂደዋል፡፡ ጠዋት 4፡00 ላይ ጋሞ ጨንቻ ሀላባ ከተማን ገጥሞ 2ለ0 አሸንፎ ወጥቷል፡፡ በጉዳት ረጅም ጊዜን ለክለቡ ግልጋሎት ሳይሰጥ የከረመው እና በቅርቡ ወደ ሜዳ የተመለሰው ንጋቱ ፀጋዬ እና ልማደኛው አሸናፊ ተገኝ የጨንቻን የድል ግቦች ከመረብ አሳርፈዋል፡፡

ጨዋታዎች ከሰዓትም ቀጥለው በፋይናንስ ቀውስ ውስጥ እየዳከረ የሚገኘው እና በተደጋጋሚ ቅሬታ የሚሰማበት ወላይታ ሶዶ ከተማ ከኢኮሥኮ ጋር ያለ ጎል ሲያጠናቅቁ ሀምበሪቾ ዱራሜን ከ ጅማ አባቡና ያስተናገደው የምድቡ የዛሬ የመጨረሻ ጨዋታ በሀምበሪቾ 1ለ0 አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡ ማሊያዊው የቀድሞው የአባ ጅፋር እና ባህርዳር የመሀል ተከላካይ አዳማ ሲሶኮ በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃ ለክለቡ ግብ ያስቆጠረ ተጫዋች ነው፡፡

በምድብ ሐ በሁለተሓው ዙር የመጀመርያ ሳምንት ሊደረግ የነበረውና በኮሮና ውጤት በጊዜ አለመድረስ ምክንያት ያልተከናወነው የቡታጅራ ከተማ እና ቂርቆስ ጨዋታ ዛሬ ተከናውኖ አንድ አቻ ተጠናቋል። ጆን ማሉማ ቡታጅራን ቀዳሚ ቢያደርግም ክብሩ ሳዲቅ በሁለተኛው አጋማሽ ቂርቆስን አቻ አድርጓል።


© ሶከር ኢትዮጵያ