ሊግ ካምፓኒው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየምን ተመልክቷል

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ አምስት ሳምንታት ጨዋታዎችን የሚያስተናግደው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በዛሬው ዕለት በሊግ ካምፓኒው አመራሮች ግምገማ ተደርጎበታል፡፡

አሁን በድሬዳዋ እየተከናወነ የሚገኘው ውድድር ከ10 ቀናት በኋላ ወደ ሀዋሳ አምርቶ የሚቀጥል ሲሆን ለዚህ ይረዳ ዘንድም የሊግ ካምፓኒው አመራሮች በሀዋሳ ከተማ በመገኘት የተዘጋጁትን መሠረተ ልማኖች እና ውድድሩን የሚያስተናግደው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሜዳን ቃኝተዋል፡፡ በምልከታው ወቅት የሊግ ካምፓኒው የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ፣ ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ፣ የውድድር እና ሥነ ስርዓት ክፍል ኃላፊው ዶ/ር ወገኔ ዋልተንጉስ እና የሊግ ካምፓኒው የቦርድ አባል አቶ አንበሴ መገርሳ በተጨማሪም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን፣ የሲዳማ ክልል ስፖርት ኮሚሽነር አቶ ፍሬው አራርሶን፣ የክልሉ እግርኳስ ፌዴሬሽን ም/ፕሬዝዳንት አቶ አንበሴ አበበ ተገኝተዋል።

የሊግ ካምፓኒው በዋነኝነት የመጫወቻ ሜዳው ምን ይመስላል የሚለውን የተመለከተ ሲሆን የተጫዋቾች መቀየሪያ፣ መታጠብያ እና መፀዳጃ ክፍሎች፣ የሱፐር ስፖርት የጨዋታ አስተላላፊዎች የሚጠቀሙበት ቦታ ምቹነት ተመልክተዋል፡፡ ከስታዲየሙ ምልከታ በተጨማሪ የተዘጋጁ ስድስት የልምምድ ሜዳዎች እና ክለቦች ሊያርፉባቸው የሚችሉትን ሆቴሎችም ተቃኝተዋል።

የሊጉ የበላይ አካል ከዚህ ቀደም እንዲሰሩ ጥቆማ የተሰጠባቸው አብዛኛዎቹ ሥራዎች መሰራታቸውን ሲናገሩ የተደመጠ ሲሆን በጥቂት ቀናት ውስጥ መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች ግን በፍጥነት መስተካከል እንዳለባቸው ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡


የሊግ ካምፓኒው ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ በሀዋሳ ዝግጅት ዙርያ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ከሞላ ጎደል ሀዋሳ ለውድድሩ ዝግጁ እንደሆነች ተናግረዋል። “የተወሰኑ ጉድለቶችን ተመልክተናል። ነገር ግን ብዙ ልፋት ሳይሆን ጥቂት ሥራ የሚጠይቁ ናቸው። እነዚህ በፍጥነት እንዲሰሩ ለአዘጋጆቹ ነግረናል። ለምሳሌ ሜዳው የተወሰነ ቦታ ላይ ውሀ ይይዛል፤ ይሄን እንዲያርሙ ነግረናቸዋል። ሰላሳ ጨዋታ የሚያስተናግድ ሜዳ በመሆኑ ለሜዳው ትኩረት ስጡት ብለናል። ይሄ የመጨረሻ ምልከታችን ነው፤ የሀዋሳ ዝግጅት በቂ በመሆኑ ውድድሩ ይደርግበታል። ከዚህ በኋላ የአስር ቀናት ጊዜ ስላለ በቀሩት ጊዜያት ሥራዎች ተሰርተው ይጠናቀቃሉ፤ ውድድሩም ከሚያዚያ 28 ጀምሮ ይካሄዳል የሚል እምነት አለን።” ብለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ