በትግራይ ክልል መቀመጫቸውን ያደረጉ ሦስቱ ክለቦች የጋራ ውይይት ሊያደርጉ ነው

ዘንድሮ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ላይ ሳይሳተፉ የቀሩት በትግራይ ክልል የሚገኙት ሦስቱ ክለቦች በአመራሮቻቸው በኩል ስብሰባ ሊቀመጡ ነው።

መቐለ ሰባ እንደርታ፣ ወልዋሎ እና ሱሑል ሽረ በወቅታዊው ሀገራዊ ሁኔታ ምክንያት በዘንድሮው የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ተሳታፊ አለመሆናቸውን ተከትሎ ሊጉ በአስራ ሦስት ክለቦች መካከል መካሄዱ ይታወቃል። በቀጣይ ዓመት ዳግም ወደ ውድድሩ ይመለሳሉ ወይስ ሊግ ካምፓኒው ባወጣው የመፍትሄ ሀሳብ መሠረት የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ተደርገው ለከርሞ በአስራ ስድስት ክለቦች ይቀጥላል የሚለው የብዙ የስፖርት ቤተሰቦች ጥያቄ ሆኗል።

በቅርቡ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን መቀመጫቸውን ትግራይ ካደረጉ ሦስቱ ክለቦች ጋር መገናኘት መጀመሩን መዘገባችን ይታወቃል። አሁን በደረሰን መረጃ መሠረት ደግሞ በዚህ ሳምንት መጨረሻ የትግራይ ክልል ስፖርት ኮሚሽንና የትግራይ ክልል እግርኳስ ፌዴሬሽን እንዲሁም የሦስቱ ክለቦች አመራሮች በተገኙበት ስብሰባ ሊቀመጡ እንደሆነ ሰምተናል። በውይይታቸውም በዋናነት በቀጣይ ዓመት ወደ ውድድር የሚመለሱበትን መንገድ እንዴት እንደሚሆን ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በዚህ ጉዳይ የሚኖሩ አዳዲስ ነገሮችን እየተከታተልን የምናቀርብ መሆኑን ከወዲሁ እንጠቁማለን።