ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ወሳኙን ጨዋታ አሸንፎ ለኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፎ በእጅጉ ተቃርቧል

በ25ኛ ሳምንት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ ሁለተኛ ደረጃን ለማግኘት ወሳኝ የነበረው የኢትዮጵያ ቡና እና ሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ በቡናማዎቹ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ የቡና ቡድን አባላት የሊጉን በአንድ የውድድር ዓመት የጎል ሪከርድ ያሻሻለው አቡበከር ናስርን ምስል እና 27+ እንዲሁም እንኳን ደስ አለህ የሚል መልዕክት የያዘ ቲሸርት በመልበስ የተቀበሉት ሲሆን እንደተለመደው የጨዋታው ዋነኛ ርዕስ ሆኖ ቡናን ወደ ድል መርቷል።

ጨዋታው ግብ ማስተናገድ የጀመረው ገና በመጀመርያው ደቂቃ ነበር። ዊልያም ሰለሞን ከሆሳዕናዎች የተነጠቀውን ኳስ ይዞ በመግባት ከግራ መስመር ሲያሻግር ሀብታሙ ታደሰ ጨርፎት ግቦ ጠባቂው ቢመልሰውም በተቃራኒ የጎል ጠርዝ ላይ የነበረው ሪከርድ ጎል አስቆጣሪው አቡበከር ጋር ደርሳ በቀላሉ ወደ ጎልነት ቀይሯታል።

ከጎሉ በኋላም በእንቅስቃሴ የተሻሉ የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በርካታ የጎል ዕድል ባይፈጥሩም ወደ ተጋጣሚ የጎል ክልል መድረስ ችለው ነበር። በ21ኛው ደቂቃ ላይ ከሀብታሙ ታደሰ በጥሩ ሁኔታ የተሻገረለትን ኳስ አቡበከር ናስር በተከላካዮች መሐል ተቆጣጥሮ በግብ ጠባቂ አናት ላይ ቢያሳልፍም ጥንካሬ ያልነበረው በመሆኑ በተከላካዮች የወጣችው ኳስ ልዩነት ልታሰፋ የምትችል ነበረች።

ኳሱን ለቡና በመተው በፈጣን መልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ እድል ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ሆሳዕናዎች በ7ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት በዳዋ ሆቴሳ አማካኝነት ጠንካራ ሙከራ ሞክረው ተክለማርያም ያዳነበት የመጀመርያ ሙረራቸው ሲሆን በቀጣይ ደቂቃዎች ዳዋ ሆቴሳ ፊት አውራሪነት አደጋ መፍጠር ችለዋል። በ43ኛው ደቂቃ ላይም ከአማኑኤል ዮሐንስ ላይ የነጠቁትን ኳስ ዳዋ ወደፊት በመገስገስ ያመቻቸውን ኳስ ዱላ መትቶ ተክለማርያም ሲተፋው ወጣቱ ደስታ ዋሚሾ አግኝቶ ቡድኑን አቻ አቆይተናል።

በሁለተኛው አጋማሽ በመጀመርያው እንደነበረው የቡና የኳስ ቁጥጥር ወደ ጎል ዕድልነት ያልተቀየረ ሲሆን እና በጥብቅ ተከላክለው በመልሶ ማጥቃት የሚጫወቱት ሀዲያ ሆሳዕናዎችም ወደ ቡና የሜዳ ክፍል የገቡባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት ነበሩ በዚህም ውሀ እረፍት ድረስም የጠራ የጎል ዕድል መመልከት ሳንችል ቆይተናል።

ከውሀ እረፍቱ በኋላ መጠነኛ መሻሻል ያሳየው ጨዋታው ሙከራዎች እና ጎል ተመልክተንበታል። በሒደት ወደ ግራ አዘንብሎ ወደ ውስጥ ሰብሮ በመግባት አደጋ ሲፈጥር የነበረው አቡበከር ናስረሰ በ75ኛው ደቂቃ ላይ ከታፈሰ ሰለሞን የተቀበለውን ድንቅ ኳስ በግሩም አጨራረስ የውድድር ዓመቱ 29ኛ ጎሉ አድርጓታል።

ወደ መሪነት ከተሸጋገሩ በኋላም ማጥቃታቸውን የቀጠሉት ቡናዎች በ82ኛው ደቂቃ ልዩነታቸውን ሊያሰፉበት የሚችሉትን ዕድል አምክነዋል። ዊልያም ሰለሞን ጎል ለማስቆጠር ጥሩ አቋቋም ላይ ሆኖ ያገኘውን ኳስ መትቶ ወደ ውጪ ወጥቶበታል።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የአቻነት ጎል ለማስቆጠር ጥረት ያደረጉት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ከቆመ ኳስ አደጋዎች መፍጠር ችለው ነበር። በተለይ ከማዕዘን ምት ተሻምተው በረከት ወልደዮሐንስ የገጫቸውና በተክለማርያም ሻንቆ የተመለሱበት ሙከራዎች የሚጠቀሱ ነበሩ።

ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና 2-1 መጠናቀቁን ተከትሎ ቡናማዎቹ ነጥብቸውን አርባ በማድረስ ለኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፎ ከመጨረሻው ጨዋታ አንድ ነጥብ ብቻ ሲጠብቁ ሰበታ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና ከፉክክር ውጪ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።