የሴካፋ የምድብ ድልድል የሚወጣበት ቀን ታውቋል

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የሚከናወነው የሴካፋ ውድድር የምድብ ድልድል የሚደረግበት ቀን ተገልጿል።

ከሰኔ 26 እስከ ሐምሌ 12 በባህር ዳር ከተማ የሚደረገው የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ ውድድር አስራ አንድ የቀጠናው እና አንድ ተጋባዥ ሀገራትን እንደሚያሳትፍ ይጠበቃል። በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ብሔራዊ ቡድኖችም ለተጫዋቾቻቸው ጥሪ እያቀረቡ ዝግጅት ማድረግ ይዘዋል። ከደቂቃዎች በፊት በወጣ መረጃ መሠረትም ደግሞ የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ እግርኳስ ማኅበር የውድድሩን የእጣ ማውጣት መርሐ-ግብር የፊታችን አርብ እንደሚያደርግ ይጠቁማል። የሴካፋ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አውካ ጋቻዮ እንደገለፁት ከሆነ የእጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓቱ በዙም (ኦንላይን) እንደሚከናወን ለአባል ሀገራት ማስታወቃቸውን አውስተዋል።

ከ23 ዓመት በታች ተጫዋቾች ብቻ በሚሳተፉበት በዚህ ውድድር ላይ (ሦስት ከ23 ዓመት በላይ የሆኑ ተጫዋቾች ይፈቀዳሉ) አስራ አንድ ሀገራት (ከሩዋንዳ በስተቀር) ለመሳተፍ ማረጋገጫ መስጠታቸው ታውቋል። እስከ ትናንት ድረስ ማረጋገጫ ያልሰጠው የሩዋንዳ እግርኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ሪጊስ ኡዋይዙ ግን እስከ ዛሬ ምሽት ድረስ ብሔራዊ ፌዴሬሽናቸው በውድድሩ መካፈል እና አለመካፈላቸውን ማረጋገጫ እንደሚሰጥ ተናግረዋል። በተያያዘ ዜናም በትናንትናው ዕለት የሩዋንዳ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለሴካፋ ውድድር የቀድሞውን የራዮን ስፖርት ጊዜያዊ አሠልጣኝ ሶስቴን ሀቢማናን ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ አድርገው መሾሙ ተሰምቷል።