ፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡና አህጉራዊ ውድድራቸውን የሚጀምሩበት ጊዜ ታውቋል

በቀጣይ ዓመት ከኢትዮጵያ በአህጉራዊ የውድድር መድረክ የሚሳተፉት ፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡና የውድድር ጊዜያቸውን አውቀዋል።

የአፍሪካ እግርኳስ የበላይ የሆነው ካፍ የ2021/22 የቻምፒየንስ ሊግ እና የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ውድድሮች ከመቼ ጀምረው እንደሚደረጉ ይፋ አድርጓል። በዚህም የቀጣይ ዓመት ውድድሮች የቅድመ ማጣርያ ጨዋታዎች ከጳጉሜ አምስት (ሴፕቴንበር 10 /21) ጀምሮ እንደሚከናወኑ ተመላክቷል። የመልስ ጨዋታዎች ደግሞ ከሳምንት በኋላ የሚደረጉ ይሆናል። የማጣሪያ ጨዋታዎች (የአንደኛ እና የሁለተኛ ዙር) ከተጠናቀቁ በኋላም የምድብ ጨዋታዎች ከየካቲት ወር (ፌብሩዋሪ) ጀምሮ መደረግ እንደሚጀምሩ ተጠቁሟል።

በካፍ ደረጃ መሠረት 12 ሀገራት (አልጄሪያ፣ አንጎላ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ግብፅ፣ ጊኒ፣ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያ፣ ቱኒዚያ እና ዛንዚባር) በ2021/22 የቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ሁለት – ሁለት ተሳታፊ ክለቦችን እንደሚያቀርቡ ተገልጿል። ሀገራችን ኢትዮጵያም ፋሲል ከነማን በቻምፒየንስ ሊግ ኢትዮጵያ ቡናን ደግሞ በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ እንደምታካፍል ይጠበቃል። በተገለፀው መሠረትም ቡድኖቹ ከጳጉሜ አምስት ጀምሮ የመጀመሪያ ዙር የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታቸውን የሚያከናውኑ ይሆናል።

ሁለቱ ቡድኖች ወደ ተከታዩ ዙር የሚያልፉ ከሆነ በሁለተኛው የቅድመ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታ ከጥቅምት 5-7 / የመልስ ጨዋታ ደግሞ ከጥቅምት 12-14 እንደሚያደርጉ የወጣው መርሐ-ግብር ያሳያል።

ፋሲል ከነማ ከሁለተኛው ቅድመ ማጣርያ ከወደቀ ወደ ኮንፌሬሽን ዋንጫ ምድብ ድልድል ለመግባት ጨዋታ የሚያደርግ ሲሆን ከኅዳር 17-19 (የመጀመርያ) እንዲሁም ከኅዳር 24-26 (የመልስ) ጨዋታውን ያከናውናል።

በተያያዘ ዜና ካፍ ውድድሮቹ ከሚደረግባቸው ቀናት በተጨማሪ ቡድኖች የሚያስመዘግቧቸው ተጫዋቾችን ቁጥር ከ30 ወደ 40 ለማሳደግ የወሰነ ሲሆን በጨዋታ ላይ የሚቀየሩ ተጫዋቾች ቁጥርንም ከሦሰት ወደ አምስት ማሳደጉን አስታውቋል። በተጠባባቂ ወንበር ላይ የሚቀመጡ ተጫዋቾች ቁጥርም ከሰባት ወደ ዘጠኝ እንዲያድግ ተደርጓል።

በውድድሮቹ ክለቦች ተጫዋቾችን የሚመዘግቡበትም የምዝገባ ቀነ ገደብ ደግሞ እስከ ነሐሴ 9 እንዲሆን ተወስኗል።