የስድስቱ ክለቦች ውድድር የመክፈቻ ጨዋታ እስካሁን አልጀመረም

የትግራይ ክልል ክለቦችን በሁለተኛው አማራጭ ውድድር ለመተካት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ዛሬ በሚጀምረው ውድድር 3:00 ላይ ሊደረግ የነበረው የመክፈቻ ጨዋታ በሁለት ምክንያቶች ዘግይቷል፡፡

ሁለቱ ክለቦች ወደ ዩኒቨርሲቲው ቅጥር ጊቢ ቢደርሱም ከአንድ ሰዓት በላይ ለመቆም ተገደዋል፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች በሀዋሳ ሲደረጉ በጊቢው ለነበሩ ሰራተኞች እና የጥበቃ አካላት ክፍያን መፈፀም ሳይችሉ በመቅረታቸው ወደ በተያዘው ሰዓት ወደ ውስጥ እንዳይገቡ መደረጉ ተገልጿል፡፡ ይሁን እንጂ የሲዳማ ክልል ባደረገው ጥረት ወደ ስታዲየሙ ክለቦቹ የገቡ ሲሆን ለጨዋታው ዝግጁ ለመሆን ወደ መልበሻ ክፍል ገብተዋል፡፡

ሁለተኛው የመዘግየቱ ምክንያት ደግሞ ለዚህ ውድድር የተዘጋጀው አወዳዳሪ ኮሚቴ በሰዓቱ ሜዳውን ለሚያዘጋጁ አካላት ሜዳው ለጨዋታ ብቁ እንዲሆን ወቅቱን በጠበቀ መልኩ መናገር ባለመቻላቸው ሜዳው የሳር ማጨድ እና መሰል ሥራዎች እየተሰሩበት በመሆኑ ሊዘገይ ችሏል፡፡

አስቀድሞ ዝግጅት መደረግ ሲገባው እንከኖች ከጅምሩ የታየበት ይሄ ጨዋታ ከደቂቃዎች በኃላ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሶከር ኢትዮጵም በስፍራው የምትገኝ ሲሆን በቀጥታ ወደ እናንተ መርሀግብሩን የምታደርስ ይሆናል፡፡