ሪፖርት | አዳማ ከተማ ወሳኝ ሦስት ነጥብ አሳክቷል

ወንድማማቾችን በተቃራኒ ያፋለመው የአዳማ ከተማ እና ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከ ጨዋታ አዳማን በሰፊ የጎል ልዩነት አሸናፊ አድርጓል።

በመጀመሪያው የውድድሩ ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክን አንድ ለምንም የረቱት አዳማ ከተማዎች ሦስት ነጥብ ካገኙበት ጨዋታ አንድ ተጫዋች ብቻ ለውጠው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በዚህም አሠልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ታፈሰ ሰርካን አሳርፈው ሠይፈ ዛኪርን ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ አካተዋል። እንደ አዳማ ሁሉ በመጀመሪያው ጨዋታ ድል አድርገው ለዛሬው ፍልሚያ የተዘጋጁት ኮልፌዎች በተመሳሳይ አንድ ለውጥ ብቻ አድርገዋል። በዚህም አሠልጣኝ መሐመድኑር ዳዊት ቹቹን ተክቶ ተመስገን ዘውዱ ወደ ሜዳ እንዲገባ አድርገዋል።

እስከ 15ኛው ደቂቃ ድረስ ምንም የግብ ሙከራ ያልተደረገበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ጅማሮ ላይ ኮልፌዎች ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ሲሞክሩ አዳማዎች ደግሞ ተጋጣሚያቸው በኳስ ቅብብል ውስጥ ሆኖ የግብ ማስቆጠሪያ ክፍተት እንዳያገኝ ሲታትሩ ታይቷል። ከላይ በጠቀስነው ደቂቃ ላይ ግን ጨዋታው የመጀመሪያውን ሙከራ አስተናግዶ ግብ ተቆጥሯል። በዚህም የኮልፌው ተከላካይ አቡበከር ካሚል ኳስ ለግብ ጠባቂው አዲስኪዳን ኪዳነማርያም አደጋን በሚጋብዝ ሁኔታ ሲያቀብለው የግብ ዘቡ ወደ ኋላ የተመለሰለ ኳስ ማፅዳት ተስኖት ኳስ የግቡን መስመር አልፋ አዳማዎች መሪ ሆነዋል።

ጨዋታው ቀጥሎ 27 ደቂቃ ላይ ዳግም ወደ ኮልፌ የግብ ክልል ያመሩት አዳማዎች ተጨማሪ ጎል ለማግኘት ተቃርበው ነበር። በዚህ ደቂቃም ማማዱ ኩሊባሊ ከሠይፈ ዛኪር የተሻማለትን ኳስ ለበላይ ዓባይነህ አቀብሎት ግብ ሊቆጠር ሲል ተካላካዮች ተረባርበው ኳሱን አውጥተውታል። ኳስን እንደ መቆጣጠራቸው የግብ ዕድሎችን በተሻለ መፍጠር ያልቻሉት ኮልፌዎች ጠጣሩን የአዳማ የኋላ መስመር ማለፍ ተስኗቸው ታይቷል። ይልቁንም ደቂቃ በደቂቃ እድገት እያሳዩ በመጡት አዳማዎች የጨዋታውን የሀይል ሚዛን ተነጥቀው ለመጫወት ተገደዋል። በአጋማሹም ምንም የግብ ሙከራ ሳያደርጉ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽለው የቀረቡ የሚመስለው ኮልፌዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ መታተር ይዘዋል። ገና አጋማሹ በተጀመረ በሁለተኛው ደቂቃም ሀቢብ ከማል ወደ ቀኝ ባዘነበለ ቦታ ላይ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ በመላክ ቡድኑን አቻ ለማድረግ ጥሯል። ለተሰነዘረባቸው ጥቃት ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ያሰቡ የሚመስለው አዳማዎች ከደቂቃ በኋላ መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ ሊያደርጉ ነበር። በዚህም ሚሊዮን ሠለሞን ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ በላይ በግንባሩ ለመግጨት ቢጥርም ኳስ ዒላማዋን ስታ ወደ ውጪ ለጥቂት ወጥታለች።

ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው ጨዋታውን ማድረግ የቀጠሉት አዳማዎች በ60ኛው ደቂቃ በጥሩ መናበብ ወደ ኮልፌ ሜዳ አምርተው ነበር። ነገርግን በጥሩ ቅብብል የተገኘውን የመጨረሻ ኳስ የደረሰው ኤሊያስ አህመድ ኳሱን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። አሁንም አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ያላደረጉት ኮልፌዎች በ68ኛው ደቂቃ የቀኝ መስመር ተከላካዩ ተመስገን ዘውዱ ወደ ሳጥን መሬት ለመሬት ባሻገረው እና ደሳለኝ ወርቁ ባልተጠቀመበት ኳስ ግብ ፍለጋቸውን ቀጥለዋል።

ጨዋታው 70ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ መጥፎ ጊዜ እያሳለፈ የነበረው የኮልፌው የመሐል ተከላካይ አቡበከር ከሚል ጀሚል ያቆብ ላይ በሰራው ጥፋት አዳማ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምትም ከሦስት ደቂቃዎች በፊት ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አብዲሳ ጀማል ቢመታውም ተጫዋቹ ኳስን ከመረብ ማገናኘት ተስኖት ዕድሉ መክኗል። 

እንደ መጀመሪያው አጋማሽ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች እድገት እያሳዩ የመጡት አዳማዎች በሁለት ደቂቃዎች ውስጥ ሁለት ጎል አስቆጥረው መሪነታቸውን አስፍተዋል። በቅድሚያም ኤልያስ አህመድ ከመዓዘን የተሻገረን ኳስ ራሱን ነፃ አድርጎ በመቆም ወደ ጎልነት ሲቀይር በመቀጠል ደግሞ ጀሚል ያቆብ ከግራ የተሻገረለትን ኳስ በጥሩ ሁኔታ ተቆጣጥሮ አዲስኪዳን መረብ ላይ አሳርፎታል። ሦስቱ ጎል ያልበቃቸው አዳማዎች ጨዋታው ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው በአብዲሳ ጀማል አራተኛ ኳስ የማሳረጊያውን ጎል አስቆጥረዋል። በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ውጪ እጅግ ተበልጠው የተጫወቱት ኮልፌዎች አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታውን በሽንፈት ጨርሰዋል።

ውጤቱን ተከትሎ የስድስት ክለቦቹን ውድድር የደረጃ ሠንጠረዥ አዳማ ከተማ በስድስት ነጥቦች መምራት ቀጥሏል። በጨዋታው ሦስት ነጥብ እና አራት ጎል ያስረከቡት ኮልፌዎች በበኩላቸው የቀሪ ተጋጣሚዎችን ጨዋታ እየጠበቁ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።