​የአሠልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 4-0 ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከ

ተጠባቂው የረፋዱ ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሠልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ለሶከር ኢትዮጵያ ሰጥተዋል።

ዘርዓይ ሙሉ – አዳማ ከተማ

ስለ ጨዋታው?

የተቃራኒ ቡድን አጨዋወት ኳስን መስርቶ መጫወት ነው። እኛም ኳስን መስርተው እንዲወጡ ፈቅደን ነበር። ነገርግን እኛ ሜዳ ላይ ሲደርሱ ተጭነን ኳሱን እንቀበላቸው ነበር። እንደ አጋጣሚም ሆኖ ከእረፍት በፊት እነሱ በተሳሳቱት ኳስ ጎል አገባን። ከእረፍት በኋላ ደግሞ በተለይ 20 ደቂቃ ሲቀር ተጭኖ የመጫወት ብቃታችንን ከፍ በማድረግ ለመጫወት ሞክረናል። በዋናነት እነርሱ ኳስን ከኋላ እያንሸራሸሩ ሲጫወቱ ስለነበር ወደ መጨረሻ ድካም ውስጥ ገብተው ነበር። ይሄንን ደግሞ እኛ ለመጠቀም ሞክረናል። በአጠቃላይ ቡድኔ ባሰበው መንገድ ነው የተጫወተው። ኮልፌ ጠንካራ ቡድን ነው። ኳስ ይዞ የሚጫወት ቡድን ነው። ግን ወደ እኛ ሜዳ መጥተው እንዳይጫወቱ ከልክለናቸው ነበር። ከዚህ ውጪ ኳስ ታክቲክ ነው። በዚህም በመረጥነው መንገድ ውጤታማ ሆነናል። ቡድኔም ከጨዋታ ጨዋታ እጅግ መሻሻሎች አሉት።

በራሳችሁ የጨዋታ መንገድ ነው የተጫወታችሁት ወይስ የተጋጣሚን የጨዋታ መንገድ የተንተራሰ አጨዋወት የመረጣችሁት?

ኳስ ይዞ የሚጫወት ቡድን ብልጫ ወስዶ የሚንጫወት ከሆነ ስህተት ስለሚያሰራ እኛ አደጋን በማይፈጥር ቦታ ብቻ እንዲጫወቱ አድርገናል። ይሄንንም በሜዳ ላይ አይተናል። ስህተታቸውን ደግሞ ተጠቅመናል። ስለዚህ በራሳችን መንገድ ተጋጣሚያችንን አይተን ነው የተጫወትነው። ዞሮ ዞሮ ያሰብነውን ታክቲክ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ አድርገናል።

የኮልፌው አሠልጣኝ ‘ከጨዋታው በፊት ተጫዋቾቼን የማዋከብ ሥራ ተሰርቶብኛል’ ስለማለታቸው?

ስለዚህ ጉዳይ ምንም አላውቅም። ይሄንን አሁን ነው የምሰማው። ሜዳ ላይ የሚታየው ነገር ግን ይሄንን አያሳይም። ሙሉ ለሙሉ የአቅም ጉዳይ ነው። አዳማም በአቅሙ ነው ያሸነፈው። ዳኝነትም ሆነ ሌላ ነገር ኖሮት አይደለም ጎሎቹ የገቡት። ግቦቹን በእንቅስቃሴ በልጠን ነው ያገባናቸው። ስለዚህ ይሄ ምክንያት አሳማኝ አይደለም።

መሐመድኑር ንማ – ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከ

ስለ ጨዋታው?

ጨዋታው እንደጠበቅነው አይደለም። ምክንያቱም ትናንት ወኪሎች ዶርም ድረስ በመምጣት ተጫዋቾቹን በተለያየ መልኩ በመደለል እንዳይረጋጉ አድርገዋል። የባለፈው ቡድናችን እና የዛሬው አንድ አይደለም። ተጫዋቾቹ አዳማ እና የተለያየ ክለብ እንደሚገቡ በመንገር አምሯቸው ከቁጥጥር በላይ እንዲሆን አድርገዋል። እኛ ይሄንን ነገር ማታ እንደሰማን ተጫዋቾችን በተናጥል እየጠራን ለማናገር ሞክረናል። ጨዋታውም ወሳኝ እንደሆነ ለመንገር ሞንረናል። ግን አልሆነም።

ሜዳ ላይ የነበረውስ ብልጫ እንዴት የመጣ ነበር?

እንዳልኩት ትላንት ነው ሥራው የተሰራው። በአምሮ ተጫዋቾቹ ለጨዋታው እንዳይዘጋጁ አድርገዋል። እንደምታቀው ደግሞ ኳስ ይዞ የሚጫወት ቡድን በአምሮ ነው የሚጫወተው። የእኛም ቡድን በአምሮ የሚጫወት ቡድን ነው። ስለዚህ ችግሩ ትላንት የተፈጠረ ነው። ለጨዋታውም መበላሸት የትላንቱ ነገር ትልቅ ቦታ ነበረው። የምናውቀውን እንቅስቃሴ እንኳን መተግበር አልቻልንም። ቡድኔ ዛሬ ባዶ ነበር። ስለዚህ ዋናው ችግር የትላንቱ ክስተት ነው።

ስለ ቀጣይ ጨዋታዎች?

የተፈጠረውን ነገር ለማስተካከል ስራዎችን ለመስራት እንሞክራለን። ተጫዋቾቹንም በማናገር ወደ ነበረን ነገር ለመመለስ እንጥራለን።