ሴካፋ 2021 | ዩጋንዳ ለሴካፋ ውድድር ዝግጅት ሳውዲ አረቢያ ገብታለች

በሴካፋ ውድድር ላይ ትልቅ ስም ያላት ዩጋንዳ በቀጣይ ሳምንት በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ለሚጀምረው ውድድር የሚጠቅማትን ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች ለማድረግ ወደ ሳውዲ አረቢያ አቅንታለች።

አስራ አንድ የቀጠናው እንዲሁም አንድ ተጋባዥ በአጠቃላይ አስራ ሁለት ሀገሮችን እንደሚያሳትፍ የሚጠበቀው የ2021 የምስራቅ እና መካከለኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ከነገ በስትያ እንደሚጀምር ቀድሞ ቢነገርም በአንዳንድ ተሳታፊ ሀገራት በሌላ ውድድር ላይ መሳተፍ እና የዝግጅት ጊዜ ማጠር ምክንያት የውድድሩ የመጀመሪያ ቀን ለሁለት ሳምንት እንዲገፋ ሆኗል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በውድድሩ ለመሳተፍ ቀድመው ለተጫዋቾቻቸው ጥሪ ካቀረቡ እና ዝግጅት ከጀመሩ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ለተጨማሪ ዝግጅት ወደ ሳውዲ አረቢያ ማቅናቱ ታውቋል።

የወቅቱ የሴካፋ ውድድር አሸናፊ የሆነው ዩጋንዳ ከሳምንት በፊት ለ35 ተጫዋቾች ጥሪ አቅርባ በካምፓላ በሚገኘው ክሬንስ ፓራዳይዝ ሆቴል መቀመጫውን በማድረግ ዝግጅት ጀምሮ ነበር። ካሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ ደግሞ ቡድኑ ወደ ፉፋ ቴክኒካል ሴንተር በመዘዋወር የውድድሩን መጀመር ሲጠባበቅ ነበር። የውድድሩ መራዘም በሳምንቱ መጀመሪያ ከተሰማ በኋላ ደግሞ ብሔራዊ ቡድኑ የዝግጅት ጊዜውን በሳውዲ አረቢያ ለማድረግ ወደ ስፍራው በረራ ማድረጉ ታውቋል።

በሳውዲ አረቢያ እግርኳስ ማኅበር በተሸፈነው የብሔራዊ ቡድኑ ጉዞ 25 ተጫዋቾች እና 10 የአሠልጣኝ ቡድን አባላት እንደተካተቱ ተነግሯል። በኳታር አውሮፕላን ኪው አር 1386 ከኢንቴቤ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የተነሳው ልዑካኑም ትናንት ምሽት በሪያድ ከተማ በሚገኘው ኪንግ ካሊድ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በሠላም መድረሱ ተረጋግጧል። ልዑኩ ሪያድ ከደረሰ በኋላም ቆይታውን ወደሚያደርግበት ኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል አምርቷል። እየወጡ ባሉ መረጃዎች ከሆነ ብሔራዊ ቡድኑ በሪያድ ልምምድ ከማድረግ በተጨማሪ ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን (ነገ እና ሰኞ) ከሳውዲ አረቢያ ብሔራዊ ቡድን ጋር እንደሚያደርግ ተመላክቷል።