ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስድስት ተጫዋቾችን አስፈርሟል

በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የዞን የማጣሪያ ውድድር ላይ የሚሳተፈው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስድስት አዲስ ተጫዋቾችን የግሉ ማድረጉ ተሰምቷል።

በኢትዮጵያ የሴቶች እግርኳስ ላይ ትልቅ ስም ያለው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቀናት በፊት ውላቸው ያለቀውን አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ቆይታ ለቀጣዩቹ ሁለት ዓመታት ካራዘመ በኋላ ፊቱን ወደ ተጫዋቾች አዙሯል። በዚህም የህይወት ደንጊሶ፣ ዓለምነሽ ገረመው፣ ፎዚያ መሐመድ እና ንግስቲ መዓዛን ውል አራዝሞ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል። የዝውውር መስኮቱ በዛሬው ዕለት እንደተከፈተ በተሰማ መረጃ ደግሞ ቡድኑ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ መቀላቀሉ ታውቋል።

ቡድኑን የተቀላቀለችው የመጀመሪያ ተጫዋች መዲና ዐወል ናት። የቀድሞ የቅድስተ ማርያም ዩኒቨርስቲ እና መከላከያ የአጥቂ መስመር ተጫዋች የነበረችው መዲና በሊጉ ላይ ካሉ ምርጥ ተጫዋቾች መካከል አንዷ እንደሆነች ይታወቃል። እንደ መዲና ሁሉ በቴክኒክ ረገድ ከላቁ ተጫዋቾች አንዷ የሆነችው የምስራች ላቀውም የቡድኑ ፈራሚ ነች። የቀድሞ የአርባምንጭ፣ መከላከያ እና አዳማ ከተማ የአማካይ መስመር ተጫዋች የምስራች ከመዲና ጋር በመሆን ለቡድኑ የተለየ ግብዓት እንደምትሆን ይጠበቃል።

ሦስተኛዋ የቡድኑ ፈራሚ የግብ ዘቧ ታሪኳ በርገና ናት። ታሪኳ የዓመቱ ኮከብ ግብ ጠባቂ ሆና የተመረጠች ሲሆን ጥቂት ግብ ካስተናገዱ ግብ ጠባቂዎችም ቀዳሚዋ ሆና የዘንድሮውን የውድድር ዘመን ማገባደዷ ይታወሳል። እንደ ታሪኳ ሁሉ ድንቅ የውድድር ዓመት ያሳለፉት የተከላካይ መስመር ተጫዋቾቹ ሀሳቤ ሙሳ እና ትዝታ ኃይለሚካኤልም መዳረሻቸው ባንክ ሆኗል። የቀድሞ የዳሽን ቢራ እና ጥረት ኮርፖሬቷ ተከላካይ እና ያለፉትን ሁለት ዓመታት በድሬዳዋ ያሳለፈችው ሀሳቤ እንዲሁም የሀዋሳ ከተማዋ ትዝታ በተመሳሳይ ጥሩ ዓመት ማሳለፋቸው ታይቷል።

ቡድኑን የተቀላቀለችው የመጨረሻዋ ተጫዋች የአጥቂ መስመር ተጫዋቿ ፀጋነሽ ወራና ናት። የቀድሞ የአርባምንጭ ከተማ አጥቂ ፀጋነሽ ዘንድሮ ከድሬዳዋ ጋር ጥሩ ዓመት ማሳለፏ ተስተውሏል። በግሏም ስምንት ግቦችን ለቡድኑ ማስቆጠሯ አይዘነጋም። አሁን ደግሞ ጉዞዋን ወደ አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ክለብ በማዞር የእግርኳስ ህይወቷን ቀጥላለች።

አምስቱ ተጫዋቾች የሁለት ዓመት ውል ሲፈርሙ ከሀዋሳ ከተማ ቡድኑን የተቀላቀለችው ትዝታ ኃይለሚካኤል ብቻ ግን የአንድ ዓመት ፊርማ ማኖሯን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘው መረጃ ያመላክታል።