አርባምንጭ ከተማ ሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የአስር ነባሮችን ውል አድሷል

ዘንድሮ ከከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ የበላይ በመሆን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደጉን ያረጋገጠው አርባምንጭ ከተማ ሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የአስር ነባሮችን ውል ለተጨማሪ ዓመት አደሰ፡፡

ሀቢብ ከማል ክለቡን የተቀላቀለ የመጀመሪያው ተጫዋች ሆኗል፡፡ በአጥቂ መስመር ላይ በኢትዮ ኤሌክትሪክ ዘንድሮ ደግሞ በኮልፌ ቀራኒዮ ያሳለፈ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በመለያ ውድድር ለኮልፌ ቀራኒዮ እየተጫወተ ይገኛል።

አሸናፊ ተገኝ ሌላኛው የክለቡ አዲስ ተጫዋች ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በአርባምንጭ ከተማ የተጫወተው አሸናፊ ዘንድሮ በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ለ ለጋሞ ጨንቻ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ የነበረ ሲሆን የቀድሞው ክለቡን ዳግም ተቀላቅሏል፡፡

ሦስተኛው ተጫዋች ፋሲል አበባየሁ ነው፡፡ በጌዴኦ ዲላ በአማካይ ስፍራ ሲጫወት የቆየው ይህ ተጫዋች ለአሰሌጣኝ መሳይ ተፈሪ ስብስብ ጥልቀት ለመጨመር አዲስ ፈራሚ ሆኖ ተቀላቅሏል፡፡

ከሦስቱ አዲስ ተጫዋቾች በተጨማሪ በክለቡ የነበሩ አስር ነባር ተጫዋቾች ውል ማደሱን የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ስንታየው ንጉሤ በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ በክለቡ ረዘም ላለ ጊዜ በመጫወት ያሳለፈው አምበሉ ወርቅይታደስ አበበ፣ የቀድሞው የደደቢት እኢ ኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም ያለፉትን ሦስት ዓመታት በትውልድ ከተማው አርባምንጭ እያሳለፈ የቆየው ሌላኛው ተከላካይ ተካልኝ ደጀኔ፣ ወላይታ ድቻን በአጋማሽ ዓመቱ ለቆ ወደ ቀድሞ ክለቡ ያመራው ሁለገቡ ፀጋዬ አበራ ካራዙሙት መካከል ሲጠቀሱ በተጨማሪም ይስሀቅ ተገኝ (ግብ ጠባቂ)፣ አንድነት አዳነ (ተከላካይ)፣ አንዱዓለም አስናቀ (አማካይ)፣ በላይ ገዛኸኝ (አጥቂ)፣ አብነት ተሾመ (አማካይ)፣ አሸናፊ ኤልያስ (የመስመር አጥቂ) እና መላኩ ኤልያስ (ተከላካይ) ውል አድሰዋል፡፡

የክለቡ ሥራ አስኪያጅ የአጥቂው ራምኬል ሎክን ውል ለማደስ በንግግር ላይ እንዳሉ የገለፁልን ሲሆን በሀዋሳ የማሟያ ውድድር እየተመለከቱ የሚገኙት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪም ከፕሪምየር ሊግ ክለቦች ሰባት አዳዲስ ተጫዋቾችን ሊያስፈርሙ በንግግር ላይ መሆናቸውን ኃላፊው አያይዘው ገልፀውልናል፡፡