አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ በዐፄዎቹ ቤት ውላቸውን አድሰዋል

ፋሲል ከነማን የ2013 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮን ያደረጉት አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ለተጨማሪ ዓመት ውላቸውን አድሰዋል፡፡

ፋሲል ከነማን ከ2012 የውድድር ዘመን ጀምሮ ተረክበው ማሰልጠን የጀመሩት የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ የየመኖቹ አልሳቅር፣ አህሊ ታይዝ፣ አል ቲላል እና ዋህዳሰንዓን አሰልጥነው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በአዲስ አበባ ከተማ፣ ሰበታ ከተማ እና መከላከያ ከሰሩ በኋላ ወደ ፋሲል ከነማ በማምራት በሁለተኛ ዓመት የዐፄዎቹ ቤት ቆይታቸው የ2013 ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግን ለመጀመሪያ ጊዜ አሸናፊ እንዲሆን አድርገዋል፡፡

አሰልጣኝ ሥዩም ሰኔ ሠላሳ ላይ በክለቡ የነበራቸው ውል በመጠናቀቁ ከተለያዩ ክለቦች እና የመን ብሔራዊ ቡድን ጋር ስማቸው ሲያያዝ ቢቆይም በጃኖ ለባሾቹ ቤት ለአንድ ተጨማሪ ዓመት እንደሚቆዩ ዕርግጥ ሆኗል፡፡ “በብዙ ፈተና ውስጥ ያለፍኩበት ክለብ ነው፡፡ በዚህ ዓመት ከእኔ በተሻለ ቻሌንጅ የተደረገ አሰልጣኝ የለም። ራሴን በምወደው ደጋፊ ፊት በድጋሚ ለመታየት ዕድሉን ማግኘት በመቻሌ ደስተኛ ነኝ። ቡድኑ ከፊቱ ትልቅ ውድድር አለበት፤ የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ። በዚህ ውድድር ራሴን ለመፈተን በመፈለግ እና ክለቡን ወደተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ በማሰብ ነው ለአንድ ዓመት ውሌን ያራዘምኩት።” በማለትም አሰልጣኙ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በትናንትናው ዕለት አብዱልከሪም መሐመድን ያስፈረመው ፋሲል ተጨማሪ ተጫዋቾች ለማስፈረም በድርድር ላይ እንዳለ የተጠቆመ ሲሆን በጳጉሜ ወር የቻምፒዮንስ ሊግ የማጣሪያ ጨዋታ ያለው ቡድኑ በያዝነው ወር አጋማሽ ወደ ዝግጅት እንደሚገባም ሰምተናል፡፡