አዳማ ከተማ አዲስ አሰልጣኝ አግኝቷል

ወደ ፕሪምየር ሊጉ ውድድር በድጋሚ የመመለስ ዕድልን ያገኘው አዳማ ከተማ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝን ቀጥሯል፡፡

የ2013 ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግን በአሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤል እየተመራ እስከ ዓመቱ አጋማሽ ድረስ መዝለቅ ቢችልም ክለቡ ባስመዘገበው ደካማ ውጤት የተነሳ ከአሰልጣኙ ጋር በመለያየት በምትኩ አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉን በመተካት ዓመቱን ቢያጠናቅቅም ወደ ከፍተኛ ሊጉ ለመውረድ መገደዱ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ የትግራይ ክልል ክለቦች በሊጉ ካልተሳተፉ እነሱን ለመተካት በሀዋሳ በተደረገው የማሟያ ውድድር ላይ በአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ መሪነት አንደኛ ደረጃ ይዞ በመጨረስ ለቀጤይ ዓመት ተሳትፎ ማረጋገጫ እየጠበቀ ይገኛል፡፡

ከውድድሩ መጠናቀቅ በኃላ ከአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ጋር ክለቡ ለመቀጠል ፍላጎት ቢያሳይም አሰልጣኙ ወደ ሀዋሳ ከተማ በመጓዛቸው ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ በዛሬው ዕለትም የክለቡ ቦርድ ባደረገው ውይይት አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝን ምርጫቸው ማድረጋቸውን የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ አንበሴ መገርሳ በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስን ረዘም ላሉ ዓመታት በረዳት አሰልጣኝነት እና በተለያዩ ወቅቶች በጊዜያዊ አሰልጣኝነት ያገለገሉት አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ከ2010 እስከ 2011 ክረምት ድረስ ደግሞ የአሰልጣኝ አብረሀም መብራቱ ረዳት በመሆን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ማገልገል የቻሉ ሲሆን ከ2012 ጀምሮ ደግሞ የጣና ሞገዶቹ ዋና አሰልጣኝ በመሆን በፕሪምየር ሊጉ ብቅ ማለታቸው ይታወሳል። በባህርዳር ቀሪ የአንድ ዓመት ውል እየቀራቸው ከሦስት ሳምንት በፊት ከክለቡ ጋር መለያየታቸው የሚታወስ ሲሆን አሁን ደግሞ ለቀጣይ ሁለት ዓመታት አዳማን የሚመሩ ይሆናል።