ባህር ዳር ከተማ ሁለት ተጫዋቾችን አስፈረመ

አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱን የቀጠረው ባህር ዳር ከተማ ሁለት ተጫዋቾችን አስፈረመ፡፡

አሰልጣኝ አብርሀም ወደ ክለቡ መቀላቀላቸውን ተከትሎ ክለቡ በርካታ ተጫዋቾችን ለማስፈረም እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን በዛሬው ዕለት ወደ ዝውውሩ ገብቶ ሁለት ተጫዋቾችን አስፈርሟል፡፡

ተመስገን ደረሰ የጣና ሞገዶቹን ተቀላቅሏል፡፡የቀድሞው የወልቂጤ ከተማ እና ጅማ አባቡና የመስመር እና የፊት አጥቂው ከ2012 የውድድር ዘመን ጀምሮ ለአባጅፋር ሲጫወት የቆየ ሲሆን በተለይ ዘንድሮ ጅማ አባጅፋር በሊጉ ደካማ የውድድር ዓመትን ቢያሳልፍም በግሉ ድንቅ እንቅስቃሴን ከማድረግ ባለፈ ዘጠኝ ግቦችን ከመረብ አዋህዷል፡፡ ከአጥቂነት በተጨማሪ በተከላካይነትም የሚጫወተው ሁለገቡ ተመስገን በሁለት ዓመት ውል ነው የጣና ሞገዶቹን የተቀላቀለው።

ሁለተኛው አዲስ ፈራሚ መሳይ አገኘሁ ነው፡፡ ከወላይታ ድቻ የታዳጊ ቡድን 2010 ላይ ማደግ ቢችልም እስከ 2011 ድረስ በክለቡ ብዙም የመሰለፍ ዕድል ማግኘት ያልቻለው ሁለገቡ ተጫዋች በዘንድሮው የውድድር ዘመን ግን በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ሁሉ ጥሩ ጊዜን ማሳየቱን ተከትሎ በብዙ ክለቦች ተፈላጊ ቢሆንም አምስተኛ ወላይታ ድቻን የለቀቀ ተጫዋች ሆኖ ባህር ዳር ደርሷል፡፡