ሀድያ ሆሳዕና ሁለት ተጫዋቾችን አስፈረመ

በፌዴሬሽኑ ዕግድ ቢጣልባቸውም በዝውውሩ እየተሳተፉ የሚገኙት ሀድያ ሆሳዕናዎች የተከላካይ እና አማካይ ስፍራ ተጫዋቾችን አስፈርመዋል።

ፍሬዘር ካሣ ከአዲስ ፈራሚዎቹ አንዱ ነው። በቅዱስ ጊዮርጊስ እግርኳስን በመጀመር በክለቡ በቀኝ እና መሐል ተከላካይነት ካገለገለ በኃላ ወደ ድሬዳዋ አምርቶ ያለፉትን ሦስት ዓመታት ለምስራቁ ክለብ በመጫወት ያሳለፈው ፍሬዘር በዛሬው ዕለት ወደ ሀድያ ሆሳዕና ማምራቱ ተረጋግጧል፡፡

ሌላኛው ክለቡን የተቀላቀለው ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን ነው፡፡ የቀድሞው የንግድ ባንክ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች በ2009 ወደ ሀዋሳ ከተማ በማምራት በክለቡ ሁለት ዓመታት ተጫውቶ በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ቡናን ተቀላቅሎ ያለፉትን ሁለት ዓመታት በመጫወት ቆይታ አድርጓል። አሁን ደግሞ በሀዋሳ 2010 ላይ ረዳት አሰልጣኝነት ካሰለጠነው ሙሉጌታ ምህረት ጋር በድጋሚ የተገናኘበትን ዝውውር ፈፅሟል፡፡

ከወላይታ ድቻ አስፈርሞት የነበረውን አጥቂው ስንታየው መንግስቱን በድጋሚ ለድቻ አሳልፈው የሰጡት ነብሮቹ አጥቂው ፀጋዬ ብርሀኑን ከወላይታ ድቻ የመስመር ተከላካዩ ብርሀኑ በቀለን ከሀዋሳ ከተማ በቅርቡ ማስፈረማቸው ይታወሳል፡፡