አዳማ ከተማ ሁለት ተጫዋቾችን አስፈረመ

በቅርቡ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝን የሾመው አዳማ ከተማ ሁለት አጥቂዎችን አስፈርሟል፡፡

የ2013 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግን በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ሆኖ የጨረሰው እና የትግራይ ክልል ክለቦችን ለመተካት በተደረገው የሀዋሳ ውድድር በመሪነት አጠናቆ በድጋሚ ወደ ፕሪምየር ሊጉ መመለሱን ያረጋገጠው አዳማ ከተማ በዛሬው ዕለት ወደ ዝውውሩ በመግባት ሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን ማስፈረሙን የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ አንበሴ መገርሳ በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡

ዳዋ ሆቴሳ ወደ ቀድሞ ክለቡ ተመልሷል፡፡ከናሽናል ሲሚንት ከተገኘ በኃላ በቅዱስ ጊዮርጊስ በመጫወት በትልቅ ደረጃን ኳስን መጫወት የቻለው ዳዋ በፈረሰኞቹ ቤት የነበረው ቆይታ ካጠናቀቀ በኋላ በአዳማ ከተማ ረዘም ያለውን የእግር ኳስ ቆይታን ከዚህ ቀድም ማድረግ ችሏል፡፡ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ክለቡን ለቆ ወደ ሀድያ ሆሳዕና በማቅናት በተለይ በነብሮቹ ቤት ጥሩ ጊዜን ያሳለፈ ሲሆን በድጋሚ ወደ ከአንድ አመት በኋላ ወደ ቀድሞ ክለቡ ተመልሷል፡፡

ሌላኛው ፈራሚ አጥቂው አሜ መሐመድ ነው፡፡ የቀድሞው የጅማ አባ ቡና አጥቂ በክለቡ በነበረው ጥሩ ብቃት ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደ ዳዋ ሁሉ አምርቶ መጫወት የቻለ ሲሆን ከክለቡ ጋር ልክ የዛሬ ዓመት ከተለያየ በኃላ ወደ ወልቂጤ ከተማ በማምራት የ2013 አመተ ምህረት ካሳለፈ በኃላ አዲሱ የአዳማ ፈራሚ በመሆን በዛሬው ዕለት ክለቡን ተቀላቅሏል፡፡