ቡናማዎቹ የወሳኝ ተጫዋቻቸውን ውል አድሰዋል

የወሳኝ ተጫዋቻቸውን ውል ለማደስ ረዘም ያለ ድርድር ላይ የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በመጨረሻም ውጥናቸው ፍሬ አፍርቶ ተጫዋቹ ውሉን አራዝሟል።

ለተጨማሪ ዓመት ውሉን ያደሰው የቡድኑ ተጫዋች አሥራት ቱንጆ ነው። የ2010 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከመጀመሩ በፊት ከጅማ አባጅፋር የመዲናውን ክለብ ኢትዮጵያ ቡናን የተቀላቀለው አሥራት ቱንጆ ከዓመት ዓመት እየጎለበተ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች እየሆነ መጥቷል። ወደ ቡና ሲመጣ የአማካይ መስመር ተጫዋች የነበረው አስራት በቡናማው መለያ ወደ መስመር ተከላካይ ተቀይሮ እጅግ ጥሩ ብቃቱን ሲያሳይ ይታያል።

ተጫዋቹ ዘንድሮ ውሉን ማጠናቀቁን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡናዎች ውሉን እንዲያድስ ከሳምንታት በፊት ቢጠይቁትም ውይይቱ ያለ ስምምነት ተጠናቆ ነበር። ነገርግን ተጫዋቹ ወደ ባህር ዳር ለብሔራዊ ቡድን ግዳጅ ከመምጣቱ በፊት ከኢትዮጵያ ቡና የደጋፊዎች ማኅበር ፕሬዝዳንር አቶ ክፍሌ አማረ ጋር በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ድርድር አድርጎ በአብዛኛው ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ ደርሶ ነበር። ይሄንንም ሂደት ሶከር ኢትዮጵያ ከስር ከስር እየተከታተለች መረጃዎችን ስታቀርብ ነበር። አሁን በደረሰን መረጃ ደግሞ የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ሀላፊዎች የፌዴሬሽኑ ተወካዮች ባሉበት ተጫዋቹ ውል እንዲያድስ ትናንት ከሰዓት ባህር ዳር ገብተዋል። በዚህም ተጫዋቹ እና ከአዲስ አበባ ለዚህ ጉዳይ ብለው የመጡት የክለቡ ተወካዮች በአሁኑ ሰዓት ተገናኝተው ተጫዋቹ ውሉን እንዳደሰ አረጋግጠናል።

አሥራት ቱንጆ በኢትዮጵያ ቡና እንዲቆይ የደጋፊ ማህበሩ አስተዋፆኦ ከፍተኛ የነበረ ሲሆን በተለይ ፕሬዝደንቱ ክፍሌ አማረ ተጫዋቹን ተደራድሮ በማሳመን ረገድ ትልቁን ሚና እንደተወጡ ሰምተናል።