የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና በዛሬው ዕለት ተጀምሯል

በአርባ ስድስት ክለቦች መካከል በአስራ አንድ ምድቦች ተከፍሎ የሚደረገው የ2013 የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና በዛሬው ዕለት በተደረጉ አስር ጨዋታዎች ተጀምሯል፡፡

ወደ 2014 የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ የሚያድጉ ክለቦችን የሚለየው የክልል ክለቦች ሻምፒዮና በ11 ምድቦች ተከፍሎ በአርባ ስድስት ክለቦች መካከል ከሐምሌ 18 እስከ ነሐሴ 23 ቀን 2013 በሀዋሳ ከተማ የሚደረግ ሲሆን በዛሬው ዕለትም ውድድሩ በሦስት የተለያዩ ሜዳዎች በአስር ጨዋታዎች በይፋ ተጀምሯል፡፡

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ 3፡00 ሲል የተጀመረውን የድሬዳዋው ተወካይ አሊ ሀብቴ ጋራዥ እና የአሳይታ ወረዳን ጨዋታ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ እና የፌዴሬሽኑ የውድድር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ከበደ ወርቁ በመገኘት አስጀምረውታል፡፡ የአሊ ሀብቴ ጋራዥ የበላይነት በታየበት በዚህ ጨዋታ 3ለ1 በሆነ ውጤት ተደምድሟል፡፡ ኢብሳ አብዱራህማን ሁለት ግቦችን ከመረብ ሲያሳርፍ አብዱረሺድ ፈይሰል ቀሪዋን ጎል ያስቆጠረ ሲሆን ሽንፈት የገጠመው የአፋሩ አሳይታ ወረዳ ከሽንፈት ያልታደጋቸውን ጎል ሙባረክ ሰይድ በመጨረሻ ደቂቃ ላይ ከመረብ አሳርፏል፡፡

በዚሁ ሜዳ ላይ 5፡00 ሲል የሲዳማው ተወካይ ወንዶ ገነት ከተማ የደቡቡ ቡድን ደንቦያ ከተማን በኤፍሬም ሌጋሞ ሁለት ጎሎች እና በጌታቸው ቱሴ አንድ ጎል 3-1 ረቷል፡፡ በመቀጠል የድሬዳዋው ተወካይ ገንደ ሸበል እና ሰመራ ሎጊያ ያለ ጎል 0ለ0 ሲያጠናቅቁ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የመጨረሻ ጨዋታ የሆነው የአቃቂ ማዞሪያ እና የኦሮሚያው ቡሳ ከተማ ጨዋታ 2ለ2 በሆነ አቻ ውጤት ተደምድሟል፡፡

በተመሳሳይ በሀዋሳ አርቴፊሻል ስታዲየም ከተያዘለት መደበኛ ሰዓት አርባ ያህሉን ዘግይቶ የጀመረው የአዲስ አበባው ቫርኔሮ ወረዳ 13 እና የሐረር ዩናይትድ ጨዋታ በቫርኔሮ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያ በስፍራው ተገኝታ እንደተመለከተችሁ የአዲስ አበባው ተወካይ እና ድል ያደረገው ቫርኔሎ ወረዳ 13 ሚካኤል አዱካ፣ አሊይዚ አቢዮፒን እና ቲሞቲ ህዝቄል የተባሉ የጋና እና የናይጄሪያ ዜግነት ያላቸውን ተጫዋቾችን በቡድናቸው ማካተታቸው በስፍራው የነበሩትን አካላት አስገርሟል።

በዚሁ አርቴፊሻል ሜዳ ሁለተኛ በሆነው ጨወታ አመያ ወረዳ ቦንጋ መምህራን ኮሌጅን 1ለ0 ሲረታ የአማራ ክልል ተወካይ የሆነው አዲስ ቅዳም ከድንቅ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ጋር ገንደ ተስፋን በደረጀ ካሳሁን የመጨረሻ ደቂቃ ጎል 1ለ0 አሸናፊ ሆኗል፡፡ ከተበተነበት በድጋሚ መቋቋም የቻለው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቀደሞው የሀዋሳ ከተማ የተስፋ ቡድን አጥቂ አቤሴሎም አፈወርቅ ብቸኛ ጎል የሲዳማው አለታ ወንዶን 1-0 ረቷል፡፡

ዛሬ ጨዋታ ከተደረገባቸው ሜዳዎች መካከል አንዱ የሆነው የደቡብ ኮሌጅ ሜዳ ሁለት ጨዋታዎች ተከናውነውበታል፡፡ ቦሌ ክፍለ ከተማ ድሬዳዋ 06 ቀበሌን 3ለ0 ሲረመርም አማራ ሳይንት ከደቡቡ ጋርዱላ ተገናኝተው 1ለ1 አጠናቀዋል፡፡

የዛሬ ጨዋታ ሙሉ ውጤቶች

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም

ምድብ ለ

አሊ ሀብቴ ጋራዠ 3-1 አሳይታ ወረዳ
ዳንቦያ ከተማ 1-3 ወንዶ ገነት ከተማ

ምድብ ሐ

ገንደ ሸበል 0-0 ሰመራ ሎጊያ
አቃቂ ማዞሪያ 2-2 ቡሳ ከተማ

በሀዋሳ አርቴፊሻል ሳር ሜዳ

ምድብ መ

ሐረር ዩናይትድ 1-2 ቫርኔሮ ወረዳ 13

አመያ ወረዳ 1-0 ቦንጋ መምህራን ኮሌጅ

ምድብ ሠ

አዲስ ቅዳም 1-0 ገንደ ተስፋ
አለታ ወንዶ 0-1 አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ

ደቡብ ኮሌጅ ሜዳ

ምድብ ረ

ቦሌ ክፍለ ከተማ 3-0 ድሬዳዋ ቀበሌ 06

አማራ ሳይንት 1-1 ጋርዱላ

ጨዋታው ነገም ቀጥሎ የሚደረግ ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያም በተከታታይ ውጤቶችን ወደ እናንተ የምታደርስ ይሆናል፡፡

የነገ ሰኞ ጨዋታዎች

ደቡብ ኮሌጅ ስታዲየም

ምድብ ረ

ዱከም ከተማ ከ ዱራሜ ከተማ 3:00
ቤ/ሻንጉል ፓሊስ ከ አለታ ጪኮ 5፡00

ምድብ ሀ

ቦዲቲ ከተማ ከ ጉንዶ መስቀል 8፡00
ኩምሩክ ከ ጋምቤላ ኢታንግ ከተማ 1፡00

በሀዋሳ አርቴፊሻል ስታዲየም

ምድብ ተ

ካራማራ ከተማ ከ ሐረር ፖሊስ 3፡00
ዱብቲ ከተማ ከ ወረኢሉ ለገሂዳ 5፡00

ምድብ ቀ

ምስራቅ ክፍለ ከተማ ከ ዱብቲ ወረዳ 8፡00
ጋምቤላ ዐቢይ አካዳሚ ከ ሸንኮር ወረዳ 10፡00

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም

ካማሺ ከተማ ከ ዋልያ ድሬ 3፡00
ሀሁ አዲስ ከተማ ከ ሊሙ ገነት ከተማ 10፡00

ምድብ ሸ

መንጌ ቤኒሻንጉል ከ ምህረት 5፡00
ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ከ ዋግ ኽምራ 8፡00