አዳማ ከተማ ሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾችን አስፈረመ

በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ መሪነት ወደ ዝውውሩ የገባው አዳማ ከተማ አዲሱ ተስፋዬ እና ዮናስ ገረመውን አስፈርሟል፡፡

ሦስተኛ አዲስ የክለቡ ፈራሚ በመሆን አዳማ የደረሰው ተከላካዩ አዲሱ ተስፋዬ ነው፡፡ የቀድሞው የስልጤ ወራቤ፣ ወላይታ ድቻ እና መከላከያ ተጫዋች ጦሩን ከለቀቀ በኃላ ያለፉትን ሁለት የውድድር ዓመታት በሰበታ ከተማ ቆይታን ያደረገ ሲሆን ውሉም በክለቡ መጠናቀቁን ተከትሎ ለአዳማ ፊርማውን አኑሯል፡፡

ሌላኛው ፈራሚ የመስመር አጥቂው ዮናስ ገረመው ነው፡፡ከሀላባ ከተማ ከተገኘ በኃላ በኢትዮጵያ ቡና፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ንግድ ባንክ፣ ጅማ አባጅፋር፣ መቐለ 70 እንደርታ እንዲሁም የዘንድሮውን የውድድር ዓመት እስከ ዓመቱ አጋማሽ በትግራይ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር የተነሳ ሳይጫወት ከቆየ በኃላ በመጋቢት ወር ወደ ሲዳማ ቡና አምርቶ ከቀድሞው አሰልጣኙ ገብረመድህን ሀይሌ ጋር የግማሽ ዓመት የዕድሜ ቆይታን ካደረገ በኃላ በሁለት አመት ውል ለአዳማ ፈርሟል፡፡ ተጫዋቹ ከጅማ አባጅፋር እና መቐለ 70 እንደርታ ጋር የሊጉን ዋንጫ ማንሳቱም ይታወሳል፡፡