ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ድሬዳዋ ከተማ የአሰልጣኟን ውል ሲያድስ አራት አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈረመ

ድሬዳዋ ከተማ የአሰልጣኝ ብዙዓየሁ ጀምበሩን ውል ሲያራዝም ሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችንም አስፈርሟል።

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ጥሩ የውድድር ዘመን ካሳለፉ ክለቦች አንዱ ድሬዳዋ ከተማ ነው፡፡ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ለክለቡ ቦርድ ከአንድ እስከ አምስተኛ ለማጠናቀቅ ቃል ገብታ የነበረችው አሰልጣኝ ብዙዓየሁ ጀምበሩ በቃሏ መሠረት አምስተኛ ደረጃን ይዛ በማጠናቀቋ ውሏ ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት እንዲራዘምላት ያደረገ ሲሆን አራት አዳዲስ ተጫዋቾችንም ወደ ስብስቡ አካቷል፡፡

የአማካይ እና የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቿ ሰናይት ባሩዳ ወደ ምስራቁ ክለብ አምርታለች፡፡ የቀድሞዋ የደደቢት እና ንግድ ባንክ እንዲሁም የ2013 የውድድር ዘመንን በአርባምንጭ ከተማ ያሳለፈችው ባለ ልምዷ ተጫዋች የመጀመሪያ የድሬዳዋ ፈራሚ ሆናለች፡፡

ሌላኛዋ ሰናይትን ተከትላ ከአርባምንጭ ከተማ ወደ ድሬዳዋ ከተማ ያመራችው ፈጣኗ አጥቂ ሰርካለም ባሳ እንዲሁም በአቃቂ ቃሊቲ በግሏ ጥሩ ጉዞ የነበራት የመሐል ተከላካይዋ ገነት ፈርዳ እና የአማካይ ስፍራ ተጫዋቿ ቻይና ግዛቸው ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለከተማ ወደ ወደ ድሬዳዋ በአንድ ዓመት ኮንትራት ያመሩ አዳዲስ ተጫዋቾች ሆነዋል፡፡