ሲዳማ ቡና የቅድመ ውድድር ዝግጅት የሚጀመርበት ቀን ታውቋል

በ2014 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚሆን የሚጠበቀው ሲዳማ ቡና በቀጣዩ ሳምንት ዝግጅቱን እንደሚጀመር ታውቋል

ከ2013 የውድድር ዘመን በመጨረሻ ሳምንታት ባስመዘገበው ውጤት በፕሪምየር ሊጉ መቆየቱን ያረጋገጠው ሲዳማ ቡና ለቀጣዩ ዓመት ራሱን ለማጠናከር ከፍተኛ እንቅስቃሴ ያደረገ ሲሆን አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌን ለሁለት ተጨማሪ ዓመት ለማቆየት ውል ካሰሩ በኃላ ተክለማርያም ሻንቆ፣ ፍሬው ሰለሞን፣ ሙሉዓለም መስፍን፣ ተስፋዬ በቀለ፣ ቴዎድሮስ ታፈሰ፣ ብሩክ ሙለጌታ እና አንዋር ዱላን አስፈርመዋል።

የውጪ ሀገር እና የሀገር ውስጥ ተጫዋቾችን በቀጣዩ ቀናት ለማስፈረም በሒደት ላይ የሚገኘው ሲዳማ ቡና በቀጣዩ ወር የመጀመሪያ ቀናት ወደ 2014 የቅድመ ውድድር ዝግጅት ለመግባት እንደተዘጋጀ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ለሶከር ኢትዮጵያ ጠቁመዋል፡፡ የክለቡ ተጫዋቾች እና የአሰልጣኝ ቡድን አባላት በቀጣዩ ሳምንት ሐሙስ ነሐሴ 6 ከተሰባሰቡ በኃላ የሜዲካል ቴስት እና የኮቪድ 19 ምርመራዎችን አድርገው ውጤቱን መሠረት አድርጎ ከነሐሴ 8 እስከ 9 ባሉት ቀናት በሀዋሳ ከተማ ዝግጅታቸውን እንደሚጀምሩ አሰልጣኙ ጨምረው ነግረውናል፡፡