ግዙፉ አጥቂ ወደ አልጄሪያ ሊያመራ ነው

ያለፉትን ሦስት ዓመታት በፋሲል ከነማ የቆየው ሙጁብ ቃሲም የአልጄሪያውን ክለብ ሊቀላቀል ነው፡፡

እግር ኳስን በሲዳማ ቡና በአማካይ ቦታ በመጫወት የጀመረው እና በሀዋሳ ከተማ፣ አዳማ ከተማ እንዲሁም ያለፉትን ሦስት ዓመታት ደግሞ በፋሲል ከነማ የክለቡ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን እየፈፀመው ግዙፉ አጥቂ ወደ ሰሜን አፍሪካዋ ሀገር አልጄሪያ ለማምራት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መሆኑን ሶከር ኢትዮጵያ ከተጫዋቹ አረጋግጣለች፡፡

የአልጄሪያን ዋንጫ በተደጋጋሚ ያነሳው እና በ1946 የተመሰረተውና በሙሉ መጠሪያው ጄይኒስ ስፖርቲቭ ዲ ካቢሌ የሚል መጠሪያን የያዘው በአጭሩ ሲጠራ ደግሞ ጄ ኤስ ካቢሌ በሚል መጠሪያ የሚታወቀው ክለቡ ኢትዮጵያውን አጥቂ ሙጂብ ቃሲምን በሦስት ዓመት ውል ለማስፈረም ተስማምቷል ፡፡

ሙጂብ ዝውውሩን በተመለከተ “በክለቤ ፋሲል ውል ነበረኝ። ከክለቡ ጋር ይሄን ዕድል ሳገኝ ተስማምተን መግባባት ላይ ደርሰናል።” በማለት ሀሳቡን ገልፆልናል። ሶከር ኢትዮጵያ እንደተረዳችውም ተጫዋቹ ወደ አልጄሪያ የሚያደርገው ጉዞ ከወራት በፊት መጀመሩን እና ሒደቱ በመጠናቀቁ ክለቡ የአውሮፕላን ትኬት በላከለት በማንኛውም ሰዓት እንደሚጓዝ ተነግሮናል።