የጣና ሞገዶቹ ከአማካይ ተጫዋቻቸው ጋር ተለያይተዋል

ለሁለት ዓመታት በባህር ዳር ከተማ የተጫወተው የአማካይ መስመር ተጫዋቹ የአንድ ዓመት ውል ቢኖረውም ከክለቡ ጋር በስምምነት ተለያይቷል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ያደገው እና አንድ ዓመት በቡድኑ ተጫውቶ ያሳለፈው ሳምሶን 2006 ላይ አሳዳጊ ክለቡን ለቆ ወደ ደደቢት ማምራቱ ይታወሳል። በደደቢት ጥሩ ጊዜያት በማሳለፍ በ2010 ወደ ኢትዮጵያ ቡና ያመራው ተጨዋቹም ለሁለት ዓመታት በቡናማዎች ቤት ካሳለፈ በኋላ በኮቪድ ምክንያት በተሰረዘው የውድድር ዓመት (2012) ወደ ባህር ዳር ከተማ አቅንቶ ነበር።

በአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በሚመራው የባህር ዳር ቡድን ውስጥ ከአምናው ዘንድሮ የተሻለ የመጫወቻ ደቂቃ አግኝቶ ያሳለፈው ተጫዋቹ የአንድ ዓመት ውል ቢቀረውም ከክለቡ ለመለያየት ከሰሞኑን ድርድር ሲያደርግ የሰነበተ ሲሆን ድርድሩ ፍሬ አፍርቶም በትናንትናው ዕለት መልቀቂያውን ከክለቡ እንደወሰደ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።