ወጣቱ አማካይ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ተመልሷል

ወጣቱ አማካይ ከውሰት ቆይታ ተመልሶ በኢትዮጵያ ቡና አዲስ የሦስት ዓመት ውል ተፈራርሟል፡፡

በቢሾፍቱ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ማድረግ የጀመረው ኢትዮጵያ ቡና አዳዲስ እና ነባር ተጫዋቾችን በመያዝ የቀጠለ ሲሆን ከቡድኑ ጋር የሚገኘው ተስፈኛው ወጣት በየነ ባንጃውም የሦስት ዓመት ውል መፈረሙ ታውቋል፡፡ ጎዶሎሊያስ ከተባለ የሰፈሩ ቡድን ባሳየው ተስፋ ሲጪ እንቅስቃሴ ወደ አፍሮ ፅዮን ኮንስትራክሽን ከ17 ዓመት በታች ቡድን በመጓዝ በብዙዎች ዕይታ ውስጥ መግባት ችሎ ነበር። በ2010 በዩጋንዳ አስተናጋጅነት በተካሄደው የሴካፋ ከ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን በአምበልነት በመምራት እና ወሳኝ ግቦችን በማስቆጠር ቡድኑ ለፍፃሜ እንዲደርስ ካገዘ በኋላ በኢትዮጵያ ቡና ከ17 እና 20 ዓመት በታች ቡድን በመጫወት አሳልፏል። ተጫዋቹ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በኢትዮጵያ ቡና የተስፋ ቡድን ውል የነበረው በመሆኑ በውሰት ውል በከፍተኛ ሊጉ ክለብ ኢኮሥኮ አምርቶ አሳልፏል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ከክለቡ ጋር በቢሾፍቱ በልምምድ ላይ የሚገኘው ተጫዋቹ በኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ፅህፈት ቤት በመገኘት ለቀጣዮቹ ሦስት አመታት በክለቡ የሚያቆየውን አዲስ የውል ኮንትራት መፈራረሙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡