ፋሲል እና ቡና የአህጉራዊ ውድድር ተጋጣሚያቸውን ነገ ያውቃሉ

በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ውድድር የሚሳተፉት ፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡና የመጀመሪያ ዙር የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታቸውን ከማን ጋር እንደሚያደርጉ ነገ ያውቃሉ።

በተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ 54 እና 41 ነጥቦችን በመያዝ አንደኛ እንዲሁም ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁት ፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡና ከፊታቸው ላለባቸው አህጉራዊ ውድድር ዝግጅት ማድረግ ከጀመሮ ቀናቶች ተቆጥረዋል። የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ፋሲል ባህር ዳር ላይ በትናንትናው ዕለት ልምምድ መስራት ሲጀምር ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ከሳምንት በፊት ወደ ቢሾፍቱ በማቅናት ዝግጅት ማድረጉን ተያይዞታል።

ሁለቱን የክለቦች አህጉራዊ ውድድሮች በበላይነት የሚመራው ካፍም አባል ሀገራት ህጋዊ መመዘኛውን የሚያሟሉ ክለቦችን እስከ ማክሰኞ ድረስ እንዲያሳውቁት ቀነ ገደብ ሰጥቶ ነበር። በውድድሮቹ ለመሳተፍ የተመዘገቡት ክለቦች ሙሉ ለሙሉ ከታወቁ በኋላ ደግሞ ካፍ የእጣ ማውጣት መርሐ-ግብሩን ለማከናወን ሌላ ቀጠሮ ይዟል። በዚህም ነገ ነሃሴ 7 በግብፅ ካይሮ በሚገኘው የካፍ ዋና መስሪያ ቤት የሁለቱ ውድድሮች የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ድልድል እንደሚወጣ ተገልጿል።

ነገ የመጀመሪያ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ድልድል ከወጣ በኋላም በግብፁ አል አህሊ ክብር የሚገኘውን የቻምፒየንስ ሊግ እንዲሁም በሞሮኮው ራጃ አትሌቲክ ክለብ ስር የሚገኘውን የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ክብር ለመተካት የሚደረገው የአዲሱ የውድድር ዓመት ፍልሚያ ጿጉሜ 5 (ሴፕቴምበር 10) በመጀመሪያ ዙር የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች እንደሚጀመር ተመላክቷል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ውድድር አንድ አንድ ክለቦችን እንደምታሳትፍ የሚታወቅ ሲሆን ከዚህ ቀደም ባመጡት የተሻለ ውጤት በካፍ የተሻለ ደረጃ ያላቸው እና ከደቡብ አፍሪካ፣ አልጄሪያ፣ አንጎላ፣ ዲሚክራቲክ ኮንጎ፣ ግብፅ፣ ጊኒ፣ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያ፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያ፣ ቱኒዚያ እና ዛምቢያ የሚመጡ ክለቦች ግን በውድድሮቹ ሁለት ሁለት የመሳተፊያ ቦታ እንዳላቸው ልብ ይሏል።